...

The African Building Platform

Feature

ድልድዩ

Wouhib Kebede
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

በ 1961 ከአሰም ወንዝ በስተሰሜን የሚገኘውና ባብዛኛው በጣሊያን ወረራ ወቅት የተከተመው የዓድዋ ከተማ ክፍል ነዋሪ ቁጥር አነስተኛ ነበር። በስተምዕራብ ወደ አክሱም፤ በስተምሥራቅ ወደ አዲግራት እና በስተሰሜን ወደ ራማ የሚወስዱት መንገዶች ከሚገናኙባት ከአነስተኛዋ የአዲ አቡን ከተማ ወደ ዓድዋ የሚወስደው ከሰባት ኪሎ ሜትር የማይበልጠው መንገድም ሕዝብ የሰፈረበት አልነበረም። አዲ አቡን (ወይም ብሎኮ – Check Point) ያንጊዜም ቢሆን የዓድዋ ከተማ አካል ተደርጋ ነበር የምትቆጠረው። እኔም በማዘጋጃ ቤቱ እየታዘዝኩ በመመላለስ ብዙ ሥራ ሠርቻለሁ።

በ 2009 የተነሳ የድልድዩ ፎቶግራፍ ይኸውና። ወንዙ አሰምን እስኪቀላቀል ድረስ አራት ተጨማሪ ድልድዮች ተሠርተውበታል፤ ወደ አልመዳ ጨርቃጨርቅ የሚወስደውን ጨምሮ። እነሆ የአንድ ድልድይ ዕድሜ ገደብ የሆነውን 50 ዓመት አልፏል።

በዓድዋና በአዲ አቡን መካከል ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚፈሰው ማይ ጉዋጉዋ የተባለ አነስተኛ ወንዝ ዓድዋ ከተማን ለሁለት ከሚከፍለው የአሰም ወንዝ ጋር ተቀላቅሎ ጉዞውን ወደ ተከዜ ይቀጥላል። ከዚህ ወንዝ በስተምዕራብ አንድ የመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም አለ። ተቋሙ ከሁለቱም ከተሞች ተገንጥሎ ያለ በመሆኑ በተለይ ማይ ጉዋጉዋ በሚሞላበት ጊዜ ወደ ዓድዋ ከተማ መምጣት የሚቻለው አዲ አቡን ሄዶ መዳረሻው አጠገብ ባለው ድልድይ ተሻግሮ ነው። ነዋሪዎች፤ መምህራንና ተማሪዎች ወደ ዓድዋ በቀጥታ የሚያደርሳቸው ድልድይ እንዲሰራላቸው የቆየ ፍላጎት ቢኖራቸውም የማዘጋጃ ቤቱ አቅም ባለመፍቀዱ ጥያቄው መልስ ሳያገኝ ቆይቷል።

ይህንን ጥያቄ የሰሙ የፒስ ኮርስ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተመረጠው ቦታ ድልድይ ለመሥራት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ስምምነት ደርሰው ሥራ ጀመሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን ማዘጋጃ ቤቱ በጉዳዩ እንዲገባበት አልተደረገም። ወጣቶቹ አሜሪካውያን በጎ ፈቃደኞች አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤታቸው ፈቃድና የተወሰነ ሥራ ማስኬጃ ያገኙ በመሆኑ ለበጎ ሥራ ሌላ የቢሮክራሲ ጉዳይ አስፈላጊ ነው ብለው አላመኑም። ሥራውን እንደጀመሩ ግን መፍትሔ የሚያሻ ጉዳይ ስላጋጠማቸው ወደ ማዘጋጃ ቤት መምጣቸው አልቀረም። የማዘጋጃ ቤቱ ሹም በጉዳዩ በቀጥታ መግባት ቀጥሎ የበጀትና ሌላም ኃላፊነት አስከትሎ መምጣቱን በማየት ይሆናል፤ በግል እንድረዳቸው ጉዳዩን ለኔ ተዉት።

አሁን ደግሞ በፍጹም የማላውቀው የሲቪል ኢንጂኒየሪንግ ሥራ ውስጥ ልገባ ነው። አላውቅም ማለት ድሮ ቀርቷል። በዚህ ላይ በዕድሜ እኩዮቼ የሆኑ ወጣቶች ውቅያኖስ አቋርጠው ሕዝብ ለመርዳት ሲተጉ፤ ምክንያት ፈልጌ ከሥራው መሸሽ ከበደኝ። በዚህ ላይ ወጣቶቹን ሳነጋግራቸው የሥራ ተነሳሽነት ብቻ እንጂ ስለምሕንድስና ያላቸው ዕውቀት ከኔ የተሻለ አልነበረም። ስለሁኔታው ስጠይቃቸው ሥራውን ገና መጀመራቸውንና መሠረቱን ለመጣል ችግር እንዳጋጠማቸው ነገሩኝ። ለማሰብ ያህል ጊዜ እንዳገኝ አጭር ቀጠሮ ሰጠኋቸውና ይህን ተግዳሮት (ቃሉ ያሁን ጊዜ ነው) እንዴት እንደምወጣ ሌላ ዙር ጭንቀት ውስጥ ገባሁ።

በቀጠሮው ቀን ወደ ቦታው ወሰዱኝና በስተምሥራቅ የሚገኘውን የድልድዩን ተሸካሚ መሠረት ለመጣል የጀመሩትን ቁፋሮ አሳዩኝ። በስተምዕራብ ያለው ተሸካሚ ግን ቦታው ዓለታማ በመሆኑ መሠረቱን ለመጣል ምን ዓይነት ዘዴ እንደሚሻል የኔን ምክር እንደሚፈልጉ ጠየቁኝ። መሠረቱ የሚጣልበት ቦታ በወቅቱ በወንዙ ተሸፍኖ ስለነበር ውሃውን መጥጦ ማየት እንደሚያስፈልግ አሳስቤ የዚያን ቀን ጉብኝት አበቃ። ፖምፕ ፈልገው እስኪመጡ ድረስ ከራሴ ጋር ተሟግቼ ምን እንደሚሻል ለመወሰን ጊዜ መግዣ እንዲሆነኝ እንጂ የአካባቢው ሁኔታ በግልጽ የሚያመለክተው ነገር ነበር። በሁለተኛው ቀጠሮ ስሄድ ውሃው ተመጥጦ፤ ድንጋዩ አግጥጦ ጠበቀኝ። ቀድሞውኑ የሚፈነቀል ድንጋይ እንደሌለ፤ ቦታው ንጣፍ ዓለት እንደሆነ ግልጽ ነበር። በዚህ ላይ ተዳፋት አለው። እላዩ ላይ ቤቶን (concrete) ቢያርፍበት አይንሸራተት ይሆን? ተጨማሪ የማሰቢያ ጊዜ ያስፈልጋል። ተጨማሪ ትዕዛዝ መስጠት አስፈላጊ ነው። ድማሚት የለ፤ የመሰረሰሪያ መሣሪያ የለ፤ ዓለቱ የማይነቃነቅ ነው። እንደዚህ መሆኑ ደግሞ መሸከም ላይ ችግር የለም ማለት አይደለም እንዴ? ትዕዛዝ ሰጠሁ። መሠረቱ በሚያርፍበት ቦታ ላይ የተቻላችሁን ያህል ድንጋዩን ጥረቡና መጥቼ አየዋለሁ አልኩ። ከበጎ ፈቃደኞቹ ጋር የሚሠሩት አናጢዎችና ግንበኞች ሳያዝኑብኝ አልቀሩም።

በ 2009 የተነሳ የድልድዩ ፎቶግራፍ ይኸውና። ወንዙ አሰምን እስኪቀላቀል ድረስ አራት ተጨማሪ ድልድዮች ተሠርተውበታል፤ ወደ አልመዳ ጨርቃጨርቅ የሚወስደውን ጨምሮ። እነሆ የአንድ ድልድይ ዕድሜ ገደብ የሆነውን 50 ዓመት አልፏል።

ለሦስተኛው ጉብኝት ስሄድ፤ በአንድ በኩል 15 ሳ.ሜ ያህል በሱ ትይዩ ደግሞ 10 ሳ.ሜ. ያህል ጠርበው ጠበቁኝ። ከዚህ በላይ እንደማንሄድ እወቀው የሚል መልዕክት ከፊታቸው ላይ ይነበባል። በእግርጥም አንድ ጊዜ ልይ ብዬ አንዱ ጠራቢ ሞክሮ ሲያሳየኝ፤ ይህን ያህል መሥራታቸው የሚያስደንቅ ነበር። ዓለቱ በፍጹም የማይነቀነቅ፤ ሲጠረብ ከርሞ አንዳችም መሰንጠቅ ያላሳየ ነበር። ከንፈር ብጤ ግን ተገኝታለች። መንሸራተቱን ለመግታት በቂ ትሆን ይሆን? ሌላ ምንም ማድረግ አይቻልም። መሠረቱን መጣል ትችላላችሁ ብዬ ውሣኔዬን አሳወቅሁ። ሀሳቤን ይዤ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ከዚያ በኋላ ወደ ቦታው ተመልሼ አልሄድኩም።

እጠይቃለሁ ግን። ከአካባቢው የመጣ ሰው እንደአጋጣሚ ሳገኝ። የፒስ ኮር በጎፍቃደኞቹ ፈልገውኝ አያውቁም። እኔ እንዳልፈልጋቸው ሌላ ሥራ መጥራት ነው ብዬ አስቤ ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም ከምጠይቃቸው ሰዎች በቂ መረጃ አገኛለሁ። ድልድዩም አልቆ መኪና ጭምር እየተሻገረበት አገልግሎት መስጠት ጀመረ። በአጭር ጊዜ ማለቁ በራሱ የሚያስደንቅ ነበር። በመጠኑ የእርካታ ስሜት አደረብኝ። ትንሽ አስተዋጽዖ አድርጌያለኋ።

ማይ ጉዋጉዋ፤ ዝናብ ሲዘንብ አወራረዱ ኃይል የተቀላቀለበት በመሆኑ አደገኛ ነው። ስሙም ከዚህ አወራረድ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም። በሰውና በንብረት ላይም ጉዳት እንደሚያደርስ ሰምቼያለሁ። ቆይቶ ይህ ሃሳብ እየመጣብኝ ማሰቤ አልቀረም። የፒስ ኮር በጎፈቃደኞቹ ሥራቸውን ጨርሰው ወደሌላ አካባቢ ሄደዋል። አንድ ነገር እንኳን ቢከሰት በቅርብ የምገኘው ተጠያቂ እኔ መሆኔ አይደለም? ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ሃሳብ ይዞ ይመጣል። እንደበፊቱ በአጋጣሚ የማገኛቸውን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ከመምህራን ማሠልጠኛው አካባቢ የሚመጡ ሰዎችን ሆን ብዬ ፈልጌ ሌላ ሌላ ወሬ አዋራለሁ። የድልድዩን ስም ሳላነሳ። ሄደው ከመጡበት ደህና ነው ማለት አይደለም? ሁሌም እጠይቃለሁ። ድልድዩ ሥራውን ቀጠለ። እኔም ተልዕኮዬን ጨርሼ የሦስተኛ ዓመት ትምህርቴን እየተከታተልኩ ሳለ ሳስበው ግን የሚገርመኝ ነገር ነበር።

እንዲያው ለመሆኑ እነዚያ የፒስ ኮር በጎፈቃደኞች ዲዛይን ነበራቸው? አይመስለኝም። ዲዛይን ባይሰራ እንኳን ንድፍ እያነበበ የሚያስፈጽም ሰው ከእንደኔ ያለ ተማሪ ያንን ዓይነት ጥያቄ ይዞ መፍትሔ ፍለጋ እንዴት ይመጣል? ደግሞስ ንድፍ ኖሮ ቢያቀርቡልኝ ወይስ ሳት ብሎኝ ራሴ ብጠይቅ ኖሮ እንዴት አድርጌ አነብበው ነበር? የስትራክቸራል ዲዛይን ንድፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳዩኝ የንግሥተ ሳባ ት/ቤትን ማስፋፊያ ሊሰሩ የመጡ የሥራ ተቋራጭ ሠራተኞች ናቸው። የነገሩኝ ሁሉ አልተያዘልኝም። ይልቅስ፤ ብረት ሲያስሩ፤ ቦታ ላይ ሲደረድሩ ወይም ቤቶን ሲሞሉ የደረስኩኝ ዕለት ነገሮች ግልጽ ሆነው ይታዩኝ ነበር። ድልድዩ መቼስ ብረት ታስሮ፤ ቤቶን ተሞልቶ፤ ነው ተሰርቶ ያለቀው። ለላይኛው ሥራ (super structure) ሌላ ልዩ አዋቂ አግኝተው መሆን አለበት እነዚያ ወጣት አሜሪካውያን በጣም ባጭር ጊዜ ግንባታውን የጨረሱት። //

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© October, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.