...

The African Building Platform

Feature

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ

ህላዊ ሰውነት በሻህ
(አርኪቴክት)
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

በግንቦት ወር 1955 ዓ.ም. (እ.አ.አ. 1963 ዓ.ም.) 32 የአፍሪካ አገራት በኢትዮጵያዋ መዲና አዲስ አበባ ተሰባስበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሰረቱ። ይህንንም ታሪካዊ የምስረታ በአል እና የመክፈቻ ጉባኤ ለማጉላት በማሰብ አጼ ኃይለስላሴ በኩራት የዘመኑ ታላቅ የመገናኛ ብዙሀን በነበረው ተንቀሳቃሽ ምስል ፕሮግራሙን በማስተላለፍ ቴሌቪዥንን ለኢትዮጵያውያን አስተዋወቁ።

ቴክኖሎጂ ከተሞቻችንን እና የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤ ለዘመናት በእጅጉ እየቀየረ መቷል። ለአንድ ማህበረሰብ ስልጣኔና እድገት የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ልማት እና ከተማ እጅግ የተሳሰሩና የተቆራኙ የማዕዘን ድንጋዮች ናቸው። ባለፉት አምዶች በተከታታይ በመዲናችን አዲስ አበባ ላይ መነሻቸውን አድርገው ወደመላው የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችና ስፍራዎች የተስፋፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም በሂደቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበራቸውን ግለሰቦችን ቃኝተናል። በዚህ እና በሚቀጥሉት አምዶች በሀያኛው ክ/ዘመን በአገራችን የተስፋፉትን የመገናኛ ብዙሀን ቴክኖሎጂዎች ከቴሌቪዥን በመነሳት እንመለከታለን።

ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ታላላቅ ነገስታት ድንበሮቻቸውን ወደ ጎረቤት አካባቢዎች እንዲሁም ራቅ ወዳሉ ስፍራዎች በማስፋፋትና ቅኝ ግዛቶችን በመፍጠር የተቆጣጠሩትን ማሕበረሰብ የተፈጥሮና የሰው ሀብት በመበዝበዝ ሀይላቸውን ሲያጠናክሩ እንደነበር ከታሪክ እንረዳለን። የጥንታዊቷ ግሪክ፣ የጥንታዊቷ ሮም እና የጥንታዊቷ ግብጽ ነገስታትም በዚህ ልምምዳቸው ይታወቃሉ። በተመሳሳይ ዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ ደግሞ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአብዛኛው በአውሮፓውያን ሲካሄድ ቆይቶ፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ 1907 ዓ.ም. ላይ አውሮፓውያን የአለምን 84 በመቶ የሚሆነውን ክፍል በቅኝ ግዛት የተቆጣጠሩበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች አባቶች በከፊል

በዚህም ምክንያት ከ90 በመቶ በላይ የሆነው የአፍሪካ አህጉር በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር ወድቆ ነበር። አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ቅኝ ገዢ አገሮች በሁለቱ የአለም ጦርነቶች ተዳክመው ስለነበር ለአፍሪካ የነጻነት ንቅናቄዎቹ ምቹ ሁኔታ ፈጠረ። ከረጅም ጊዜ የአፍሪካውያን የነጻነት ትግሎች በኋላ በ1949 ዓ.ም. ጋና የመጀመሪያዋ የአፍሪካ አገር ሆና ነጻ ወጣች። ለሚቀጥሉት 35 አመታት ያህል የነጻነት ትግሎቹ ቀጥለው በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ አገዛዝ ስርዐት መፍረስን ተከትሎ ተቋጨ።

የሁለተኛው አለም ጦርነት በአፍሪካ የቅኝ ግዛት ዘመን ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ ነበር። ይህ ወቅት በአፍሪካ ቅኝ ግዛቶች እና በአውሮፓውያኑ መካከል የነበረው ግንኙነት ላይ መሰረታዊ ተጽዕኖ የፈጠረ ነበር፤ አንድም በጦርነቱ ምክንያት የምርት እና የአቅራቦት ልውውጥ በመቋረጡ፣ ሁለት ደግሞ በጦርነቱ ላይ በተለያዩ ደረጃዎች እንዲሳተፉ በመደረጉ ነበር። በዚህም ሳቢያ ለበርካታ አፍሪካውያን ከዚህ ቀደም በቅኝ ገዢዎቻቸው ላይ አይተውት የማያውቁትን ደካማ ጎን እንዲያዩና የራሳቸውን አለም አቀፍ እይታ እንዲያሰፉ እንዲሁም የአለቆቻቸውን ታላቅ ነን ባይነት እንዲጠይቁ በራስ መተማመን ፈጠረላቸው። ልክ እንደቴሌቪዥን መስኮት።

ለቴሌቪዥን ፈጠራ ዋጋውን የሚወስድ አንድ ብቸኛ ግለሰብ የለም። የቴሌቪዥን ስርጭት ከሁለተኛው አለም ጦርነት በኋላ በፍጥነት በመስፋፋት ለማስታወቂያ፣ ለፕሮፖጋንዳ እና ለመዝናኛ አገልግሎቶች ወሳኝ የመገናኛ ብዙኃን ሆነ። የመጀመሪያው ቴሌቪዥን ጣቢያ በአሜሪካ በ1920 ዓ.ም. አካባቢ የተቋቋመ ቢሆንም፣ የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ስርጭት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በአጼ ኃይለስላሴ መንግስት ከ35 አመታት በኋላ ነበር።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጀመሪያ ህንጻና ታሪካዊ የምስረታ ስብሰባው የተካሄደበት የአፍሪካ አዳራሽ

ከጦርነቱ ማግስት በርካታ አፍሪካውያን በአገራቸው መደበኛ ትምህርት ለመማር እንዲሁም በኢኮኖሚያቸው ላይ ከፍ ያለ ሚና ለመጫወት መጠየቅና መታገል ጀመሩ። የተማሩትም አፍሪካውያን አገሮቻቸውን በመሪነት ወደነጻነት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ተጫወቱ። ከእነዚህም ውስጥ ገናናዎቹ የጋናው ኩዋሜ ንክሩማ፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ፣ የታንዛኒያው ጁሊየስ ኔሬሬ፣ የሴኔጋሉ ሌዎፖልድ ሴንጎር፣ እና የናይጄርያው ናምዲ አዚኪዌ ይጠቀሳሉ። በጦርነቱ ማግስትም በእንግሊዟ የማንቸስተር ከተማ፡ የተካሄደውና፡ በጥቁር አሜሪካዊው ቻርለስ ደቧ የተመራው አምስተኛው የፓን አፍሪካን ኮንግረስ ላይ በርካታ፡ አፍሪካውያን እና ዳያስፖራዎች ተካፈሉ። የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በማጠቃለያ የአቋም መግለጫቸው ቅኝ ግዛትን በጽኑ በማውገዝና ለጥቁር አፍሪካ ሙሉ ነጻነት የሚከፈለው ዋጋ እንደሚከፈል አወጁ።

ጋና የመጀመሪያዋ ከቅኝ ቅዛት ነጻ የወጣች አገር በሆነች ማግስት በ1950 የጋና የነጻነት ክብረ በዓል ላይ ፕሬዝዳንት ኩዋሜ ንክሩማ “የጋና ነጻነት ከመላው አፍሪካ ነጻነት ጋር ካልተቆራኘ ፋይዳ ቢስ ነው” ብሎ በመናገር ለቀጣይ ለሁለት አመታት በአፍሪካ ሙሉ ነጻነት ዙርያ አህጉር አቀፍ ጉባኤዎች አካሄደ። የአፍሪካ ነጻነት አባት በመባል የሚጠራው ንክሩማ በኮንፍረንሶቹ “የተባበሩት የአፍሪካ መንግስታት” የሚለው ራዕዩን አቀረበ። ነገር ግን ሀሳቡ በአብዛኛው ተቀባይነት ባለማግኘቱና በአህጉሩ ሶስት የተለያዩ የአስተሳሰብ ጎራዎች በመፈጠራቸው የአፍሪካን ነጻነት እና የወደፊት እጣ ፈንታ አስመልክቶ የልሂቃኑ ክርክር ደራ።

ሶስቱም ጎራዎች መጠሪያቸውን የካዛብላንካው ቡድን፣ የሞኖሮቭያው ቡድን እና የብራዛቪል ቡድን በማለት ሰየሙ። እነዚህ ሶስት ቡድኖች እና፡ የእሳቤ ልዩነታቸው ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መወለድ ምክንያት ሆነ። የመጀመሪያው የካዛብላንካ ቡድን በሞሮኮ በ1961 ዓ.ም. እ.አ.አ. ተገናኝቶ ዘረኝነት፣ ቅኝ ግዛትን፣ ኒዮ ቅኝ ግዛትን እና የአህጉራዊ ሚሊታሪን ለመቃወም አቋም ያዘ። ይህ ቡድን ጋና፣ ጊኔ፣ ግብጽ፣ ማሊ፣ ሊብያ፣ ሞሮኮ፣ አልጄሪያ፣ የሚገኙበት ሲሆን ራዕዩም የተባበሩት የአፍሪካ መንግስታትን በአንድ ምንዛሬ፣ የውጭና የመከላከያ ፖሊሲ ያለው ሆኖ ለመመስረት ያለመ ነበር።

ሁለተኛው ቡድን ደግሞ በላይቤሪያዋ መዲና የተ ሰየመው የሞንሮቪያ ቡድን ነበር። ይህ ቡድን ከብራዛቪል ቡድን ጋር ተባበረ። አባላቱ፣ ላይቤሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ሶማሊያ፣ ቶጎ፣ ቱኒዝያ, ኮንጎ፣ ካሜሩን፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ አይቮሪ ኮስት፣ ቤኒን፣ ጋቦን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ማዳጋስካር፣ ሞሪያኒያ, ኒጀር፣ ሴንትራል አፍሪካ፣ ሴኔጋል፣ ቻድ እና ኢትዮጵያን አካተተ። ይህ ቡድን የአገራትን ሉአላዊነት መጠበቅ አለበት ሲል ተሟገተ። የአባላት ጣልቃ ገብነትን በጽኑ ተቃወሙ። ከምዕራባውያን ጋርም ለመተባበር ሰሩ። በወቅቱ ነጻ፡ ከነበሩት 27 አገራት ውስጥ ብዙዎቹ የዚህ ቡድን አባል ሆኑ።

ሁለቱም ቡድኖች የበለጠ አባላትን ወደራሳቸው ለማምጣት ሲሉ በ1954 ዓ.ም. ላይ ኢትዮጵያ በተናጠል በጉባኤዎቻቸው ላይ እንድትገኝ ጥሪ ላኩላት። በካይሮ እና በሌጎስ ኮንፈረንሶች ነበሩ። አጼ ኃይለስላሴም ኮንፍረንሶቹን በሁለቱ ቡድኖች መካከል ስምምነት እንዲፈጠር ለማድረግ መልካም አጋጣሚ አርገው ወሰዱት። ሌጎስ ላይ ያለው ስብሰባ ላይ በመገኘትም በቀጣይ አመት ሁለቱንም ቡድኖች ያካተተ ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ ቃል ገቡ። ኢትዮጵያ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ተቀባይ የሆነች ስፍራ ስለነበረች ያለተቃውሞ ተስማሙ።

ለግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ የአፍሪካ አቀፉ ስብሰባ ተጠራ። አዲስ አበባም እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጅት ጀመረች። መስቀል አደባባይ አካባቢ የሚገኘው፣ አሁን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስሪያ ቤት አካል የሆነው የአፍሪካ አዳራሽ ለመክፈቻ ስብሰባው ተገነባ። በተጨማሪም ለአዲስ አበባ ከተማም አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አዲስ የማዘጋጃ ቤት ህንጻ እንዲገነባላት ተደረገ። የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደተለያዩ ቦታዎች በመብረር አብዛኛዎቹን የኮንፈረንሱን ታዳሚዎች ወደ አዲስ አበባ አመጣ።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስርጭት የተላለፈበት ስቱድዮ የሚገኝበት የአዲስ አበባ፡ከተማ ማዘጋጃ

የቀድሞ የነጻነት ታጋይ አሁን ደግሞ የአገሮቻቸው መሪ የሆኑት የክብር እንግዶችም በጉባኤው ዋዜማ ቦሌ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ መግባት ጀመሩ። ብሔራዊ ትያትር አካባቢ በሚገኘውና አዲስ በተገነባው የኢትዮጵያ ሆቴል ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ አንድ በአንድ አቀኑ።

በእለተ ቅዳሜ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ስብሰባው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በቴሌቪዥን ተዘገበ። በስብሰባው ላይ በታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች የተደረጉት የተለያዩ ንግግሮች ተቀርጸው ለኢትዮጵያውያን በቴሌቪዥኑ መስኮት ተላለፉ። ጉባኤውም በአዲስ አበባና አካባቢዋ ለሚገኘው ነዋሪ እንዲሰራጭና በወቅቱ በመላው አፍሪካ ላይ እየተካሄደ ስለነበረው የነጻነት ትግልና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ በተለይም አዲሱ ትውልድ በቴሌቪዥን መስኮቱ አማካኝነት ግንዛቤ እንዲኖራቸው አደረገ።

የሁለቱ ተቋሞች ውልደት በዚህ መልኩ ተገጣጠመ። የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ስራውን ከወራት በኋላ በይፋ በመስከረም 1956 ዓ.ም. ጀመረ። በተመሳሳይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የቅኝ እና የአናሳ የነጭ ማህበረሰቦች አገዛዝን ከአፍሪካ ለማስወገድ ወሳኝና ቁልፍ ሚና ተጫወተ። ለነጻነት ታጋዮች መሳሪያዎች በማቅረብና ስልጠናዎች በመስጠት እንዲሁም ማዕቀቦች በማስጣል የበኩሉን ድርሻ ተወጣ።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደግሞ በመደበኛ ሁኔታ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲያደርግ ሆኖ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አገልግሎት ተቋቋመ። በምርቃቱ ወቅትም አጼ ኃይለስላሴ፣ “ለህዝባችን በበለጠ ትምህርት እና እውቀት ለማካፈል የሚቻልበትን ዘዴ በመሻት ለምናደርገው ጥረት ቴሌቪዥን ተጨማሪ መሳሪያ ስለሚሆን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ መርቀን ስንከፍት ደስ ይለናል፣” በማለት ተናገሩ። መደበኛ ስርጭቱን በጥቅምት ወር 1957ዓ.ም. አንድ ብሎ ለተመልካቾቹ አስተላለፈ። መደበኛ ስርጭቱም ከምሽቱ 11:30 እስከ 5:00 ሰዐት የዘለቁ የተለያዩ የዜና እና የሀገር ውስጥና የውጭ ፕሮግራሞችን ያካተተ ሆነ።

ለማጠቃለል፣ ቴሌቪዥን የአለምን ፖለቲካ በእጅጉ የቀየረ የዘመናችን ቴክኖሎጂ ነው። በአገራችንም እንዲሁ በአጼ ምንሊክ መንግስት የስልክና የቴሌኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያን ክፍለሀገሮች ለማስተሳሰርና ንጉሱ አስተዳዳሪዎቻቸውን አዲስ አበባ ተቀምጠው በጥብቅ ለመከታተል እንዳስቻለው ሁሉ፣ የአጼ ኃይለስላሴ መንግስትም የመገናኛ ብዙሀንን በከፍተኛ ሁኔታ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲ ስራ ተጠቅሞበታል። አሁን ባለንበት በአዳዲስ ፈጠራና ቴክኖሎጂ የተሞላው የመረጃ፣ የበይነ መረብ እና የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ዘመንም የከተማችን፣ አገራችንን ብሎም የአለምን ፖለቲካ ምህዳር በእጅጉ መቀየሩን ቀጥሏል። ቸር እንሰንብት!

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© October, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.