The African Building Platform

Updates

ጦር ሜዳው

Wouhib Kebede
አቶ ውሂብ ከበደ በአርኪቴክቸርና በከተማ ፕላን አነሳስ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በ1964 ከተመረቀ በኋላ በልዩ ልዩ መስክ የ50 ዓመት አገልግሎት አበርክቷል። በሕንፃ ዲዛይን ድርጅት እስከ ዋና አርኪቴክት ፤ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እስከ መምሪያ ኃላፊ ደረጃ ሠርቷል። ከዚያም ቀጥሎ በኤስ.ቢ. ኮንሰልት ድርጅት ለረዥም ጊዜ በልዩ ልዩ የፕሮጀክት ሥራዎች ላይ ተሳትፏል። በመጨረሻም የግል የአርኪቴክት ቢሮ በማቋቋም የሙያ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። አቶ ውሂብ የኢትዮጵያ አርኪቴክቶች ማኅበር መስራች ኮሚቴ አባል ሲሆን ማኅበሩን በምክትል ፕሬዚደንትነትና በዋና ፀሐፊነት አገልግሏል።
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

ከዕለታት በአንዱ ቀን፤ ከማዘጋጃ ቤቱ ሹም “በተጠየቀው መሠረት ይፈጸም” የሚል ትዕዛዝ የሰፈረበት ከአገር ግዛት ሚኒስቴር የተጻፈ ደብዳቤ ተመራልኝ። የደብዳቤው ይዘት ለ 75ኛው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ለሚደረገው ዝግጅት ጦርነቱ የተደረገበት ቦታ ፕላንና ኬሮኬ ተነስቶ እንዲላክ የሚጠይቅ ነው። የሌቨሊንግ ኢንስትሩመንት እንኳ የሌለው ማዘጋጃ ቤት ይህ ጥያቄ ሲቀርብለት እንዴት ይወጣዋል ተብሎ ታስቦ ነው በማለት ገርሞኝ የማዘጋጃ ቤቱን ሹም ብጠይቅ፤ መሐንዲሱ አንተ ነህ ምን ቢደረግ ይሻላል ብለው ጉዳዩን ወደኔው መለሱት።

አልችልም አይባልም ሲል ቀደም ብሎ ምክር የለገሰኝን የእንዳሥላሤው (ሽሬ) መሐንዲስ መንግስቱ ተፈራን (ከኤሌክትሪካል ዲፓርትመንት የተመደበ) አስታወስኩና፤ መላ ያልኩትን ሃሳብ ማውጠንጠን ጀመረኩ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተማርኩት ጂኦግራፊ በስተቀር ሌላ ምንም እውቀት የሌለኝ ሰው የካርቶግራፊ ሥራ ማከናወን ልገደድ ሆነ። ፕላን እንዲነሳ የተባለው መቼም ካርታ ነው ብዬ ደምድሜያለሁ። ኬሮኬ ደግሞ ምን ይሆን? የዚህ ቃል ትርጉሙ አልተገኘም። ቃሉ ፈረንጅኛ እንደሆነ ግን ገምቻለሁ። ፕላን አንስቼ መላክ ከቻልኩ፤ ኬሮኬውስ ሲባል የነገሩ ምንነት የሚታወቅበት አጋጣሚ ሊገኝ ይችላል። ገና ሁለት ዓመት ስላለ ሌላ ሰው እንዲሰራው ሊደረግ ይችላል የሚል ታክቲካዊ እሳቤም ነበረበት።

የማዘጋጃ ቤቱ ሹም በግድ መልስ ሊያገኙለት የሚገባውን መሠረታዊ ጥያቄ ይዤ ሳነጋግራቸው ያቀረቡት መፍትሔም ኃላፊነትን በሚመለከት ቢሮክራሲያዊ አሰራር እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ያየሁበት አጋጣሚ ነበር። ሹሙ የዛው አገር ተወላጅ እና በዕድሜም የበሰሉ ስለነበሩ እኔ ያሰብኩት በቀጥታ መልሱን ይሰጡኛል ብዬ ነበር። ጦርነቱ የተደረገበትን ቦታ አሳዩኝ አልኳቸው። ደግ፤ ወደ ዓዲ አቡን በሚወስደው መንገድ ላይ ሰፈሩን ካደረገው የሻለቃ ጦር መኮንኖች እንዲመደቡ አደርጋለሁ አሉኝ። መጀመሪያ፤ እራሳቸው አያውቁትም እንዴ ብዬ ገርሞኝ ነበር።

ከሻለቃው ጦር ሁለት መኮንኖች ተመድበው አንድ ቅዳሜ እንዳሚካኤል ከሚገኘው ከማዘጋጃ ቤቱ ቢሮ ተነስተን በምሥራቅ አቅጣጫ የእግር ጉዞ ጀመርን። ፊት ለፊታችን ግዙፉን የአምባ ሰማያታ ተራራ እያየን ስንጓዝ እዛ ድረስ የምንሄድ ከሆነ በአንድ ቀን እንደማንደርስና የምናድር ከሆነ ለምን አልነገሩንም እያልኩ ሀሳብ ውስጥ ገባሁ። በመንገዳችን ላይ አልፎ አልፎ ቆም ብለን እንድናርፍ ያደርጉ ነበር። ለምን አንቀጥልም ብዬ ጠየቅሁ። እነዚህ ቦታዎቸ ”መዕረፊ” ይባላሉ። ማንኛውም መንገደኛ እንደ ባህል ጥቂት ደቂቃ ቢሆንም ሳያርፍ አይሄድም። እውነትም በነዚህ ቦታዎች ሁሉ እኛ ከምንሄድበት አቅጣጫ በተቃራኒው የሚጓዙ ሰዎች አረፍ ብለው እናገኝ ነበር። ነገሩ ሠላምታ ለመሰጣጠትና ሌላ መረጃም ካለ ለመለዋወጥ ይረዳል።

ከጦር መኮንኖቹ በተጨማሪ ሌሎች ባላገሮች አብረውን ስለነበሩ አንዳንድ ታሪክ ይነግሩን ነበር። ዋነኛው ጦርነት ተካሂዶበታል ከተባለበት አምባ ራዕዮ አካባቢ ያሉትን ሰናድድ እና ደባድብ ስለተባሉት ቦታዎች በትግርኛ የተገጠመውንም የሰማሁትም ከነሱ ነው። በመጨረሻም አንድ አማካይ የሆነ ቦታ ላይ ቆመን መኮንኖቹ አጭር ገለጻ ሰጥተው ባላገሮቹም አክለውበት ሲያበቁ የጭንቁ ሰዓት መጣ። ከቆምንበት ቦታ ሆኖ ከፊት ለፊታችን ወደ እንትጮ አቅጣጫ ያለው ሰፊ ሜዳማ ቦታ ጣሊያኖቹ የመጡበት አቅጣጫ መሆኑ ተነገረኝ። ከዓዲ አቡን ተነስቶ የሐን አልፎ ወደ አዲግራት የሚሄደው መንገድ በሩቁ ይታየኛል። በዚያ ርቀት የቴሌፎን ምሰሶዎችም ይታዩኛል። በቴሌፎን ምሰሶዎች መካከል ያለው ርቀት 50 ሜትር ሊሆን ይችላል። እሱን ወደ ከተማ ስንመለስ አረጋግጣለሁ። ለጊዜው እነዚህን ምሰሶዎች የርቀት መለኪያ በማድረግ ሰፊ አካባቢ በወረቀት ላይ ሳልኩና ስሞች አሰፈርኩ። የከፍታ መለኪያን በሚመለከት ተነጻጻሪ ግምት በመውሰድ ለአምባ ራዕዮ ከፍተኛነቱን ለመመዝገብ በርከት ያሉ የኮንቱር መስመር ዓይነት ክቦች ሳልኩ። ለሌሎቹ ጉብታዎችም ከአምባ ራዕዮ እያወዳደርኩ ተገቢ ነው ያልኩትን የክብ ቁጥር መደብኩና ሥራዬን ጨርሻለሁ ብዬ አስታወቅሁ። የመልስ ጉዞውን ፈጠን ባለ እርምጃ ያለ ሃሳብ አገባደድን።

ካርታው በትሬሲንግ ወረቀት ተሰርቶ በማዘጋጃ ቤቱ ሹም ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ አባሪነት ወደ አዲስ አበባ ተላከ። እኔም እነ ማጌላን እንደሚስሉት የዓለም ካርታ ባይሆንም እንደ አቅሜ መጠነኛ ክብደት በመስጠት ለራሴ አንድ ቅጂ አዘጋጅቼ ስለነበር ይዤው ወደ ሦስተኛ ዓመት ትምህርቴ ተመለስኩ። በነገራችን ላይ ይህ ትረካ የሁለተኛ ዓመት ትምህርት ተገባድዶ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ለዓድዋና አክሱም ከተማዎች በመሐንዲስነት ተመድቤ በነበረበት በ1961 ዓ.ም. የተፈጸመውን የሚያወሳ ነው።

ዓድዋ 1888 እና ADWA 1896 የሚል ጎላ ያለ ጽሑፍ ያለውን ይህን ካርታ ሦስተኛ ዓመት ስቱዲዮአችን ውስጥ ለጠፍኩት። ጓደኞቼ የካርቶግራፊ ችሎታዬንና የካርታውን አስቂኝ ጎን በመተቸት፤ በተለይም የኮንቱር ክብ መስመሮች አመዳደብ ላይ በሚሰጡት አስተያየት ለብዙ ሳምንቶች ራሳችንን አዝናናንበት። ኬሮኬ ማለትም በፈረንሳይኛ ሞዴል ማለት መሆኑ ታወቀ። እንኳን ያኔ አላወቅሁ አልኩ። በመጨረሻ ግን የዲዛይን መምህራችን የነበረው ሲኞር ፉልቪ፤ ምን ለጥፈሀል ብሎ ቀረብ ሲል ርዕሱን አየና ደንገጥ ብሎ አፈገፈገ። ካርታውም ከዛ በኋላ ከተለጠፈበት ተነሳ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የክፍላችን Peter Blake ዘንድ እንደሚገኝ ይታመን ነበር።

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© May, 2023 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.