...

The African Building Platform

Updates

ግዙፍ የሕንፃ ፕሮጀክቶችን ማቀድና መተግበርን የሚመለከቱ አንዳንድ ነጥቦች

ውሂብ ከበደ
አርክቴክት
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

ግዙፍ የሕንፃ ፕሮጀክቶች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ወጪ የሚጠይቁና በአማካይ ከአራት ዓመት ያላነሰ ግዜ የሚወስዱ እንደመሆናቸው መነሻ ሃሳብ ብቻ ይዞ በራስ አከናዋኝነት አንድ ባለሀብት በቀጥታ ሊተገብራቸው የሚችሉ አይደሉም። ፕሮጀክቱ የሚያርፍበትን ቦታ በእጅ ከማስገባት ጀምሮ ግንባታው ተጠናቅቆ የሕንፃ አስተዳደር ሥርዓት እስኪዘረጋለት ድረስ የብዙ ተዋናዮች ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው።

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዓለም አቀፋዊ ትክል አሠራር፤ የግዙፍ የሕንፃ ፕሮጀክቶችን ይዘት ያጤነና መደበኛ የቴክኒክ ሰነዶቹም ይህንኑ ለማስተናገድ በሚችል መንገድ የተዘጋጁ ስለሆነ የባለሃብቶችን ሃሳብ ከግብ ለማድረስ የሚረዳ ነው። ባለሃብቶችም ሥራውን በግል አቅም ከመሞከር ወይም በተለምዶ ከሚከናወን ወጥነትና የሙያ ጥራት ከጎደለው አሠራር ይልቅ ሙያዊ መሠረትና የተፈተነ ሂደት ያለውን ዓለም አቀፋዊ ትክል አሠራር እንዲከተሉ ይመከራል።

የፕሮጀክት ሃሳብ ያለው ባለሃብት በመጀመሪያ ማድረግ ያለበት የፕሮጀክት ጽ/ቤት ማቋቋም ነው። ይህ የፕሮጀክት ጽ/ቤት እንደ ፕሮጀክቱ የክንውን ደረጃ የሚያስፈልጉት ሠራተኞች ብዛትና የሙያ ስብጥር ሊለያይ ይችላል። በአንድ ጉዳይ አስፈፃሚ ተጀምሮ ወደ ግንባታ ሥራ ሲቃረብ በምሕንድስና ባለሙያ የሚመራና አስፈላጊ የአስተዳደርና የፋይናንስ ሰራተኞች የሚመደቡለት እስከመሆን ሊደርስ ይችላል። የፕሮጀክቱ ባለቤት ግለሰብ ባለሃብት እንኳን ቢሆን ከሌላ ሥራው ለይቶ ፕሮጀክቱን ነጥሎ እንዲመራ ማድረግ በጥብቅ ይመከራል።

ባለቤቱ የአክስዮን ማኅበር፣የመንግስት ድርጅት ወይም ሌላ ዓይነት ተቋም ከሆነ ደግሞ የተቋቋመበት ዓላማ ከፕሮጀክቱ ህልውና ጋር የተያያዘ ቢሆንም እንኳን ራሱን የቻለ የፕሮጀክት ጽ/ቤት ከሌለው የሥራ መወሳሰብ እንደሚደርስበት የታወቀ ነው።

የፕሮጀክት ጽ/ቤት የቀን ተቀን ክትትል የሚደረግበትና ማንኛውም ፕሮጀክቱን የሚመለከቱ ሰነዶች በጥንቃቄ የሚያዙበት እንዲሆን ይጠበቃል። በተደራቢ ሥራነት፤ በኮሚቴ አማካይነት ወይም በያዝ ለቀቅ የሚሠራ መሆን የለበትም።

የፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ዋና ሥራዎች የፕሮጀክቱን ቦታ በእጅ ማድረግ፣ አርኪቴክት መምረጥና ፣ሥራ ተቋራጭ መቅጠር ናቸው። ከነዚህ ሦስት ሥራዎች ውስጥ የመጀመሪያው የፕሮጀክት ጽ/ቤት ከመቋቋሙ በፊት ተከናውኖ የሚገኝበት አጋጣሚ ቢኖርም፤ የቦታውን የይዞታ ሰነዶችንና ተያያዥ መረጃዎችን ተቀብሎ ማደራጀት የማይቀር ተግባር ነው።

ለሕንፃው ዲዛይን አርኪቴክት የሚመረጡ ሥራ ከቀዳሚ ሥራዎች ውስጥ በጥንቃቄ መከናወን ያለበት ተግባር ነው። ምክንያቱም የሚመረጠው አርኪቴክት ዲዛይኑን ከማዘጋጀት በተጨማሪ የግንባታውን ሥራ የሚቆጣጠርና የባለሃብቱ ዋና አማካሪ በመሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ባለሃብቱ ራሱ አርኪቴክቱን ከመምረጥ ጀምሮ ሌሎች ልዩ አዋቂ ለሚያስፈልጋቸው ሥራዎች በየጊዜው የተለያዩ አማካሪዎች ተወዳድረው የሚመርጡበትን ሰነድ ዝግጅትና የአመራረጡን ሂደት ይከታተላል።

ሥራ ተቋራጭ የመቅጠር ሂደትን በዋነኛነት የሚያከናውነው አርኪቴክቱ ቢሆንም የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል። ለግንባታው በአርኪቴክቱ የተዘጋጀውን ሰነድ የተሟላና በጥራት የተዘጋጀ መሆኑ እንዲረጋገጥ ማድረግና ይዘቱም የባለሃብቱን ጥቅም ያስጠበቀ መሆኑን ተመልክቶ ሃሳብ የመስጠት ሚናም ይኖረዋል። በዚህ ወቅት የፕሮጀክቱን ጽ/ቤት የሚመራው ኃላፊ በሳል የምሕንድስና ባለሙያ መሆን ይኖርበታል። ይህም ካልተቻለ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኝ የምሕንድስና ባለሙያ መድቦ በጊዜያዊ በሳል አማካሪ እንዲደገፍ ማድረግም ይቻላል። በግንባታው ወቅት የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ በግንባታው ቦታ ላይ ወይም በአቅራቢያ ባለ ሕንፃ ላይ ቢሆን አመቺ ይሆናል።

ከሌሎች ፕሮጀክቶች ተሞክሮ ባለሃብቱ ስላሰበው ፕሮጀክት አንዳንድ መረጃዎች ሊኖሩት ይችላሉ። ነገር ግን በእንደዚህ ዓይነት መረጃዎች ብቻ እየተመሩ ረጅም ርቀት መሄድ ከፍተኛ ጉዳት ሊኖረው ስለሚችል ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉት ግብዓቶች በገንዘብ፤ በጊዜና በሌላም ረገድ በዝርዝር ተለይተው መታወቅ ይኖርባቸውል። ይህንንም ለማድረግ እስከሙሉ የአዋጪነት ጥናት ማከናወን የሚደርስ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል። በተለይም ፕሮጀክቱ በባንክ ብድር የሚከናወን ከሆነ የግንባታውን ብቻ ሳይሆን ሙሉ የፕሮጀክት ወጪውን ያካተተ ጥናት ቢሆን ይሻላል። ይህንንም ሥራ አማካሪ አስመርጦና ተከታትሎ ማስፈፀም ከሦስቱ ዋና ዋና ሥራዎች ቀጥሎ የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የሚያተኩርበት ይሆናል። በራስ አቅም ሊገነባ ይችላል፤ ስለዚህም የአዋጭነት ጥናት አያስፈልግም ቢባል እንኳን፤ በፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የተዘጋጀ የድርጊት መርኀ ግብርና የበጀት ዝርዝር ሊኖር ይገባል። አንድ 625 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ፕሮጀክት እንደምሳሌ በመውሰድ በጊዜና በወጪ ረገድ የሚያስፈልገውን ግብዓት የሚያሳይ ጠቋሚ መረጃ ከዚህ በታች የተመለከተውን ሊመስል ይችላል።

አብዛኛውን ጊዜ የፕሮጀክት ሃሳብ ይዘው የተነሱ ባለሃብቶችን የሚያነጋግር ሰው፤ የራሳቸውን መኖሪያ ቤት የሚሠሩትን ጨምሮ፤ ፕሮጀክታቸውን እንዴት ባነሰ ጊዜ ሊገነቡ እንዳቀዱና ወጪያቸውም ምን ያህል አነስተኛ እንደሚሆን ያላቸውን ስሜት ሊገነዘብ ይችላል። እውነታውን ግን የነሱ ፕሮጀክት ከሌሎች ፕሮጀክቶች ሊለይ የሚችልበት አጋጣሚ የሌለ መሆኑ ነው። ከላይ የቀረበው ግርድፍ ዝርዝርም በአገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከእውነታው የተቀራረበ ቢሆንም ወዲያውኑ ተቀባይነት ባያገኝም በሂደት ልዩ ክትትል ተደርጎ እንኳን የተሻለ ውጤት ለማስገኘት አዳጋች ነው።

በመጨረሻም በተለምዶ አሠራር አንዳንድ ሥር የሰደዱ ግንዛቤዎችና የአሠራር መዛባቶችን በሚመለከት የተወሰኑ ነጥቦች ማጤን ያስፈልጋል።

ሀ) አርኪቴክቶችን በሚመለከት
1) የአርኪቴክት ቢሮዎች አራቱን የአርኪቴክት ክህሎቶች ሳያሟሉ ሲቀሩ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ፤
2) የአርኪቴክት የሙያ ክፍያ፥ ለባለሞያዎች በሚከፈል ደሞዝ ላይ ተመስርቶ ሳለ ብቁና ተፈላጊውን የባለሞያዎች ቁጥር ባለማሳተፍ የጥራትና የጊዜ መጓተት ማስከተል እንደሚከሰት፤
3) ከሥራ ተቋራጮች ጋር የባላንጣነትና የበላይነት መንፈስ የማሳየት ዝንባሌ ማንፀባረቅ ያለመግባባት እንዲሰፍን እንደሚያደርግ፤ የታየባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።

ለ) በፕሮጀክት ባለቤት በኩል
1) በአርኪቴክቱ በኩል የሚመደብ የሥራ ተቆጣጣሪና በባለቤቱ በተመደበው የፕሮጀክት ኃላፊ (የጽ/ቤቱ) መካከል ያለውን ልዩነት በውል ያለመረዳት፤
2) በአንድ ጊዜ የሚሄዱ ሁለት ውሎች ቢኖሩም፥ በግንባታው ውል ላይ ያሉት ወገኖች ሁለት ብቻ (ባለቤቱና ሥራ ተቋራጩ) መሆናቸውን፥ አርኪቴክቱም በግንባታው ውል የተሰጠውን ተግባር ብቻ እንደሚወጣ አለማጤን፤
3) የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ኃላፊ በሁለቱም ውሎች የተሰጠውን ተግባር እንደሌለ፥ በቴክኒክ ረገድ በተለይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት፥ ነገር ግን አርኪቴክቱም ሆነ ሥራ ተቋራጩ ሥራቸውን በሚገባ ስለመሥራታቸው ለባለቤቱ ሪፖርት ሊያቀርብ እንደሚችል፤
4) በልዩ ልዩ ወገኖችና ተዋናዮች የሥራ ኃላፊነት መደራረብ የግጭትና ያለመግባባ መንስዔ እንደሆነ፤በተደጋጋሚ ይታያሉ።

ሐ) ያለመግባባትን ለማስወገድ
1) ወደ ክስ መሄድ ከፍተኛ ወጪና የሥራ መስተጓጎል እንደሚያስከትል፤
2) የተመረጠው ያለመግባባትን የማስወገጃ ዘዴ በግንባታ ወቅት አጁዲኬተር እንዲሰየም ማድረግ መሆኑ፤ በተግባር የታየ ነው፡፡

በዚህ አጭር ጽሑፍ የተነሱትን ሃሳቦች በዝርዝር መተንተንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በሚደረግ ውይይት ማዳበር የአርኪቴክቶች ሚና እንደሚሆን በማሰብ ሲቀርብ፤ በተከታይ የአስተያየት መስጫ ጽሑፎች እንደሚዳብር ተስፋ በማድረግ ነው።

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© October, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.