...

The African Building Platform

Feature

የግምት ሥራ

ከ ውሂብ ከበደ
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጓደኞቼን በመከተል ኢንጂኒየሪንግ ኮሌጅ ገብቼ በፕሪ-ኢንጂኒየሪንግ የመጀመሪያ ዓመት መርሃ ግብር የዲስክሪፕቲቭ ጂዮሜትሪ ሁለት ኮርሶች ተከታትያለሁ፡፡ በሚቀጥለው ዓመትም ከሲቪል፤ ከኤሌክትሪካልና ከሜካኒካል ምሕንድስና እንዲሁም ከአርኪቴክቸር የቱን መምረጥ እንደሚሻል የማውቀው ስላልነበር ከአንድ ጓደኛዬ ጋር የመመዝገቢያ ወረቀት ስንቀያይር ቆይተን ወረቀቱ ሲያልቅ በመጨረሻ ወደ ሞላነው የአርኪቴክቸር ትምህርት ክፍል ገባን፡፡ እዚያም እንደ አርኪቴክቸራል ግራፊክስና ቤዚክ ዲዛይን የመሰሉ ኮርሶችን ወሰድን፡፡ የአርኪቴክቸራል ዲዛይን ውድድር በማሸነፉ በአስተማሪነት የተቀጠረው ሚስተር ቦችኮቭም ያሸነፈበትን የፓትሪያርኬት ሕንፃ ንድፎችን በትሬሲንግ ወረቀት እንድንገለብጥ በማድረግ የወለል ፕላን፤ ገጽታና ውቅርን በሚመለከት መሠረታዊ ዕውቀት አስጨበጠን።

የሁለት ዓመት ትምህርት የጨረሰ የኢንጂኒየሪንግ ኮሌጅ ተማሪ በዩኒቨርሲቲው ደንብ መሠረት ለአንድ ዓመት በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት መሳተፍ ግዴታው ስለሆነም የአድዋና የአክሱም ከተሞች መሐንዲስ ሆኜ ተመደብኩ፡፡ በምድብ ቦታዬ ስደርስ በሁለቱም ማዘጋጃ ቤቶች የምሕንድስና አገልግሎትን በሚመለከት ማንም ሌላ ሰው ስላልነበር ሃሳብ ገባኝ፡፡ ከዚህ ቀደም የሥራ ዓለም ምን እንደሚመስል አይቶ ለማያውቅና ምን እንደሚሰራ የሚመራ አለቃ ወይም የሚያዝ ኃላፊ ለሌለው ሰው ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም ቀደም ሲል ከመቀሌ እየተነሱ በየአውራጃው እየተዘዋወሩ ይሠሩ የነበሩት መሐንዲሶች ምን ሲሰሩ እንደነበር በመጠየቅ ፍንጭ አገኘሁ፡፡ እነዚህ መሐንዲሶች፤ ሲኞር ማስካሮ እና አቶ አሱሌ አያኖ፤ የጻፏቸውን አንዳንድ ጽሑፎችና ደብዳቤዎችን አነበብኩ፡፡ በተለይም ፒያኖ ሬጉላቶሬ ዲ አድዋ የሚል የደበዘዘ የከተማውን የመንገድ አዘረጋግ የሚያሳይ ኮፒ አገኘሁ፡፡ ሲኞር ማስካሮ በወቅቱ የአምስተኛ ዓመት የአርኪቴክቸር ተማሪ የነበረው የሮኮ ማስካሮ አባት ነበሩ፡፡ የመገልገያ ዕቃዎችን በሚመለከትም አንድ አሮጌ ባለ 30 ሜትር የሸራ መለኪያ ቴፕና ስድስት ያህል ቀይና ነጭ ቀለማቸው ሊጠፋ የተዳረሰ ሬንጅ ፖሎች ተፈልገው ተገኙ፡፡ መሐንዲስ መመደቡ በመሰማቱም ቀስ በቀስ ከመንገድና ከቦታ ይዞታ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች መቅረብ ጀመሩ።

ጥያቄዎቹን እንደ ዓይነታቸው አንዳንድ ጊዜ በፒያኖ ሬጉላቶሬው በመጠቀም ባብዛኛው ግን በራሴ በማገናዘብ ውሳኔ እየሰጠሁ ጥሩ የሥራ አፈጻጸም አሳየሁ፡፡ የተመደቡልኝ ሁለት ጭቃ ሹሞች፤ አቶ ጥላሁን እና አቶ ተክለ ሃይማኖት፤ በተለይ የድንበር ውዝግብ ሲኖር የተሳሳተ ውሳኔ ላይ እንዳልደርስ ያግዙኝ ነበር፡፡ በነሱና ሬንጅ ፖል በሚይዙልኝ ረዳቶች ታጅቤ በከተማው ውስጥ ስዘዋወር ሁሉም ሰው አወቀኝ፡፡ መጠሪያዬም ‘መሐንዱስ ወደይ’ ሆነ፡፡ በሁለተኛው ወር አካባቢ የማዘጋጃ ቤቱ ሹም ከመቀሌ የመጣ ትዕዛዝ ስላለ አንድ የጠላት ንብረት የሆነን ቤት ግምት እንድሰራ አዘዙኝ።
ቤቱ ወደ ሶሎዳ ተራራ መዳረሻ ላይ ከምትገኝ ኮረብታ አናት ላይ ኮርቶ የተቀመጠና የአድዋ ከተማን ከዳር ዳር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ እንደተነገረኝም በጣሊያን ወረራ ወቅት የአድዋ ከተማ አዛዥ መኖሪያ ቤት የነበረ ነው፡፡ ቤቱን ሄጄ ካየሁ በኋላ ምኑን ከምን አድርጌ ግምት እንደምሰራ ጭንቀት አደረብኝ፡፡ የቤቱ ፕላንና የምድረ ግቢው ሥራዎች ጭምር በጊዜው በጣም ያማረ ድባብ እንደነበራቸው ይታያል፡፡ ግድግዳዎቹም የመፈራረስ መልክ አይታይባቸውም፡፡ በተለይ የወለሉ ‘ግሬስ ንጣፍ’ በጥሩ ይዞታ ላይ ይገኛል፡፡ በ‘ሶሌታ’ ከተሰራው የጣሪያ ክፍል በስተቀር ሌላው ፈርሷል፡፡ በርና መስኮትም የለም፡፡ ልስንና ሌሎች የማጠናቀቂያ ሥራዎች፤ ቤቱ ወና ሆኖ ረጅም ጊዜ በመቆየቱ ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።

ልኬት መውሰድ ብችልም ንድፍ ማዘጋጀት ግን አልችልም፡፡ የንድፍ መሣሪያ የለም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የግምቱ ሥራ ማደሻውን ወጪ ለመተመን ስለሆነ፤ እንዲህ ሆኖ ይታደሳል ብሎ ዝርዝሩን ለማውጣት ምንም ፍንጭ አልነበረኝም፡፡ በዚያም ላይ ዋጋንና የግብዓት ቁሳቁሶችን በሚመለከት ከተማ ውስጥ የሚገኙ ግንበኞችና አናጢዎችን ጠይቄ ካልሆነ በቀር ሌላ አማራጭ ሊኖር አይችልም፡፡ እነዚህ ሃሳቦችን ሳውጠነጥን ጥቂት ቀናት ቆይቶ፤ ስለግምቱ ሥራ የምታነጋግረው ሰው አለ ብለው የማዘጋጃ ቤቱ ሹም እና ሌሎች ሰራተኞች እንዳ መድኃኔ ዓለም ከሚገኝ አንድ ትልቅ መኖሪያ ቤት ወሰዱኝ፡፡ ወደ ቤቱ ስንገባ ከሰፊው እልፍኝ አንድ ብስል ቀይ የሆኑ እመቤት ከመሃል ተቀምጠዋል፡፡ አብረውኝ የመጡት እጅ ሲነሱ እኔም አብሬ እጅ ነሳሁ፡፡ ቀጥሎም ሹሙ ግምቱን የሚያዘጋጀው መሐንዲስ እሱ ነው ብለው ተናገሩ፡፡ እመቤቲቱም በመገረም አዩኝና እንግዲህ ልጄ ቶሎ ብለህ ጨርስልኝ አሉኝ፡፡ ተሰናብተን እንደወጣን ግን አብረውኝ የነበሩት ሰዎች የእመቤቲቱን ማንነት ከነገሩኝ በኋላ ቤቱ የሳቸው መሆኑንና ግምቱም ከፍ እንዲል እንደሚፈለግ አሳሰቡኝ፡፡ ነገሩ ግራ የሚያጋባ ከመሆኑም በላይ በፊት የነበረኝ ጭንቀት ላይ ያሁኑ በመጨመሩ ምንም መልስ አልሰጠሁም፡፡ ውሎ ሲያድር ግን አውጥቼ አውርጄ የግምት ሥራ የመሥራት ዕውቀቱም ሆነ ልምዱ ስሌለኝ ሥራውን እንደማልሰራ ፈርጠም ብዬ ለማዘጋጃ ቤቱ ሹም አስታወቅሁ።

ከአንድ ሣምንት በኋላ ቢሮ እንዳለሁ መንግስቱ ተፈራ በድንግት ገባ፡፡ ምን እግር ጣለህ ብለው የግምት ሥራ ልሠራ ነው የመጣሁት አለኝ፡፡ መንግስቱ የኤሌክትሪካል ኢንጂኒየሪንግ ተማሪ ሲሆን እንደኔው ለኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ለእንዳሥላሤ (ሽሬ) የተመደበ ነው፡፡ ነገሩ ገርሞኝ እኔ የአርኪቴክቸር ተማሪው አልችልም ያልኩትን አንተ እንዴት እችላለሁ ብለህ መጣህ አልኩት፡፡ ባገሩ ያለነው እኛ ነን፡፡ ምንም ነገር አልችልም አይባልም ይልቅስ አብረን እንሥራ አለኝ፡፡ የሙስና ነገርም ሸቶኛል ብለው እሱ እኛን አያገባንም ብሎኝ ሥራውን በጋራ ሠርተን አስረከብን፡፡ ድፍረት ያገኘውም እነ አቶ አሱሌ አያኖ የሠሩባቸውን የግምት መዝገቦች በማግኘቱ እንደሆነ ገለጸልኝ፡፡ ከዚያ በኋላ የግምት ሥራ አንዱ መደበኛ ሥራዬ ሆነ፡፡ ከአድዋ ውጪ እስከ ዳዕሮ ተኽሊ ድረስ እየሄድኩ አገልግሎቱን ሰጥቼያለሁ፡፡ በንድፍ የተደገፈ እንዲሆንም አቶ ወልደገብርኤል የተባሉ የከተማው ዋነኛ ባለሃብት ያቀረቡትን ጥያቄ ምክንያት በማድረግ የንድፍ መሣሪያዎች ከአስመራ ገዝተው እንዲያቀርቡ አሳምኜ የተረፈው ለሌሎች ሁሉ እንዲያገልግል ተደረገ፡፡ የተገዛው ባለ ስምንት የብዕር ጫፍ ሙሉ ራፒዶግራፍ፤ አንድ ትልቅ የኢንዲያን ኢንክ ብልቃጥ፤ ቲ ስኩዌር፤ ስኬል፤ ትራያንግሎችና ሁለት ጥቅል ትሬሲንግ ወረቀት ‘ፓፒየር ካንሶን’ ከሚስተር ቦችኮቭ የተማርኩትን በሥራ ላይ እንዳውል ረዳኝ፡፡ በተለይም የሕዝቡ እጅግ ብርቱ ጥያቄ የነበረውን የባንክ አገልግሎት ለማስገኘት አገልግሏል፡፡ በከተማው መሃል የሚገኝ አንድ የተጎሳቆለና የቁሻሻ መጣያ የነበረ የጠላት ንብረት ወና ቤት መርጬ ፕላኑን በማዘጋጀት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተልኮ የመጀመሪያው የባንክ ቅርንጫፍ እንዲከፈት አስችሏል፡፡ ቅርንጫፉ ሲከፈት እኔ ወደ ሦስተኛ ዓመት ትምህርቴ ስለተመለስኩ በምርቃቱ ላይ ባልገኝም፤ ዛሬም ድረስ አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ እንደ መጀመሪያው የተተገበረ የግንባታ ፕሮጀክቴ የማየው ነው።//

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© July, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.