እጅግ የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ ፡ጓደኞች እና የስራ ባልደረቦች ፣ 34ተኛዉን የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎች ወርሃዊ ስብሰባ/architects ወርሃዊ/ ሀሙስ መስከረም 27፣2014 ዓ.ም በከቤት እስከከተማ ማእከል ተካሂዷል፡፡ በዚህ ወር የኪነ-ህንፃ ማህበሩ፤“ኪነ-ህንፃ በማህበራዊ የትስስር ገዕ ላይ” በሚል አርዕስት አቶ ዳዊት በንቲን ጋብዞ ቆይታ አድርጎ ነበር።
የኪነ-ህንፃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት በንቲ ላለፉት 30 አመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኪነ-ህንፃና ከተማ የትምህርት ክፍል በመምህርነት እንዲሁም የተለያዩ ጥናታዊ ዕሁፎችን በመፃፍና ባለፉት ሁለት አመታት ደግሞ በኢትዮጵያ እንዲሁም በአፍሪካ ዉስጥ ተገንብተዉ ስላሉ ታሪካዊ ቅርሶች፡ ህንፃዎችና የከተማ ልማቶች፤ የኢትዮጵያ ኪነ-ህንፃና ከተሜነት/Ethiopian Architecture and Urbanizm/ በሚል የማህበራዊ የትስስር ገዕ ባለሙያዉን ብሎም ማህበረሰቡን ሲያስገነዝቡ ቆይተዋል።
አቶ ዳዊት ፕሮግራሙን የጀመሩት በተለምዶ ከሚደረገዉ በተለየ መልኩ፤ ንግግራቸዉና የምልከታ ሰሌዳዎቹ በአማርኛ ቋንቋ እንደሚሆን በማሳወቅ ነበር፣ይህንንም ማድረጋቸዉ በሀገራችን በአፍ መፍቻ ቋንቋ መግባባት ለኪነ-ህንፃ ሙያዉ እድገት የሚሰጠዉን አስተዋፅኦ በመንገር ነበር “በአፍ መፍቻ ቋንቋ ኪነ-ህንፃን በምናዎራበት ጊዜ የቋንቋ ክፍተቱን እንሰብረዋለን፣ሙያዉንም ወደማህበረሰቡ እናቀርበዋለን”።
የኢትዮጵያ ኪነ-ህንፃና ከተሜነት የትስስር ገፅ፣ ከ7,800 በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን እነዚህ ተከታዮች ከ90 በላይ ከተለያዩ የአለም ሀገራት የተጠራቀሙ ናቸዉ። በዚህ ገጽ ላይ፣የተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የኪነ-ህንጻ፣የመሬት አቀማመጥ እንዲሁም የከተማ ልማት ስራዎችን ፎቶግራፎች፣የንድፍ ስዕሎች እንዲሁም የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎችን በመለየት የመረጃ ልዉዉጥ ይካሄዳል። ይህ የመረብ ቋት አሁን ቀላል ቢመስልም በጥቂት ቃላት ፍለጋ ስለማንኛዉም የኪነ-ህንጻ ስራ የተጠናቀረና የተመሳከረ መረጃ የሚሰጥ የእዉቀት ቦታ/ቋት መሆኑ ለዘመናዊ ማህበረሰብ ዘመናዊ መፍትሄዎች የሚያቀርብ ፈጣን የእድገት መንገድ ነዉ።
በድህረ-ገፁ አለም ላይ ደግሞ አንድ ጊዜ የተጋራ ነገር ለዘላለም መቆየቱ አሳታፊነትና ግልጽነትን ያረጋግጣል፤በአንድ ጉዳይ ላይ ለውጥ ለመፍጠር ከመንግስት ሃላፊዎች ይልቅ አንቂዎችና የሙያ ታጋዮች በማህበራዊ የትስስር መረቦች ቅሬታቸውን ወይም ድጋፋቸዉን በነፃነት ያንፀባርቃሉ፣ይህ ደግሞ ዜጎች በሀገራቸዉ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑና ከታች ወደላይ አስተዳደር /bottom-up governance/ እንዲተገብሩ ያደርጋቸዋል።
ይህ ግሩፕ ከተከታታይ አላስፈላጊ መልዕት ሰሪዎችና ልጥፎች የፀዳ እንዲሆን ጥብቅ የአባላት ቁጥጥር ያለዉ፣ በአባላቱ የተመሳከረ ጥሩ ይዘት ከፅሁፍ ጋር የተዋዛ ልጥፍ እንዲሁም ወቅታዊ መረጃዎችንና ተያያዥ የድህረ-ገፅ አገናኞችን/Linked website/የያዘ ነው። በነዚህና ብዙ ምክንያቶች ተመሳሳይ ይዘት ካላቸዉ ግሩፖች በጥራት የተሻለ ያደርገዋል።
በአሁን ሰዓት ከኢትዮጵያ ተነስቶ፣ ወደአፍሪካ ኪነ-ህንፃና ከተሜነት ግሩፕ ከዛም ደግሞ የማህበራዊ ገፁን ቀይሮ ወደቴሌግራም በመሄድ የኪነ-ህንፃ መረጃን በአማርኛ በማቅረብ እድገት አሳይቷል። ወቅታዊ በሆኑ የከተማ ልማትና የስነ-ህንጻ ጉዳዮች ላይ የማህበረሰቡንና የባለሙያዉን ሀሳብ፡ድጋፍም ይሁን ተቃዉሞ የሚንፀባረቅበት ቦታ ሆኗል። ለአቢይነት ያህል በአዲስ አበባ በአንዳንድ ጥንታዊ ህፃዎች ላይ የሚታየዉ የሰማያዊ ቀለም ዕድሳት በዚሁ ግሩፕ ላይ እጅግ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። ይህ ክስተት ከኛም አልፎ በጣልያን ሃገር የታወቀ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የሚፅፍ የግሩፑ አባል፡ በራሱ የድህረ-ገፅ መፅሄቱ ላይ ጉዳዩን አስነብቧል።
ይህ ግሩፕ ከተመሰረተ አንስቶ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስላሉ ኮከብ ሴትና ወንድ ህንፃ ነዳፊዎቻችንና ከተማ ገንቢዎቻችንን ማወቅ ተችሏል፤ ብዙ የሀገር በቀል የቤት አሰራር ንድፍ ስዕሎች ተካተዋል፣ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸዉ ህፃዎችና የከተማ ቦታዎች ተሰንደዋል፤ምርምሮች ተደግፈዋል፣ስልጠናዎችና ትምህርታዊ የመስክ ጉዞዎች ተደርገዋል፤ለኢትዮጵያ ኪነ-ህንፃ ታሪክ ማህበር/ኢኪታማ/ መፈጠርም አስተዋፅኦ አድርጓል።
እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ የጊዜ የይዘት የቁጥጥር ተግዳሮቶች እንዳሉት አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡ የገጽ አስተዳደር ሰዎች አለመኖር መርዛማ የሆኑ አስተያየቶችንና ልጥፎችን ለመቆጣጠር አዳጋች አርጐታል፣በድህረ-ገፁ አለም ላይ እየተለመዱ ያሉ አስነዋሪ ልማዶችን ለማስቀረት የማያቋርጥ ክትትል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
አቶ ዳዊት በዚህ መንገዳቸዉ ሁሉ በመገኘትና በመደገፍ አብረዉ የነበሩትን የኢትዮጵያ ኪነ-ህንፃ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል ተሾመን አመስግነዋል።በቦታዉ ከነበሩ ታዳሚዎችም የድጋፍ የአድናቆትና የማበረታቻ መልዕቶች ተደምጠዋል፣እኛም የ Architects ወርሃዊ ዝግጅት ክፍልና የከቤት እስከከተማ ማእከልን ለዝግጅቱ መሳካት ከልብ እናመሰግናለን።