...

The African Building Platform

Feature

የመጀመሪያዋ መኪና በኢትዮጵያ

ህላዊ ሰውነት በሻህ (አርኪቴክት)
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

አለም አሁን በምትገኝበት የመረጃ ወይም የዲጂታል ዘመን ከቴክኖሎጂ አንፃር የግንባር ቀደም ሚና ከሚይዙት ተዋንያን መካከል “የቴክኖሎጂ ወንጌላዊ” ወይም “technology evangelist” በመባል የሚታወቁት ግለሰቦች ናቸው። ይህ ግለሰብ ለአንድ ቴክኖሎጂ ቅቡልነት የሚያስፈልገውን ወሳኝ የሰው ሀብት ድጋፍ፣ እራሱ ተጠቅሞ በማሳየትና አርዐያ በመሆን የሚያሰባሰብና የሚገንባ ነው። እነዚህም ሰዎች በአብዛኛው በየድርጅታቸው የመሪነት ቦታንም ሲይዙ ይታያሉ። በአለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው ከሚጠቀሱ የቴክኖሎጂ ወንጌላውያን መካከል የአፕል ኮምፒውተር መስራች ስቲቭ ጆብስ እና የኢንተርኔት አባቶች በመባል ዕውቅና ከተሰጣቸው ጀማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ቪንቶን ሰርፍ ይገኙበታል።

በኢትዮጵያም ታሪክ ለቴክኖሎጂ መስፋፋትና ማህበረሰባዊ ቅቡልነት በመፍጠር ልክ እንደዚህ ዘመን የቴክኖሎጂ ወንጌላዊያን ከፍተኛ ሚናን ከተጫወቱ የቀድሞ መሪዎች መካከል ዋነኛና ግንባር ቀደሙ ንጉስ አፄ ምንሊክ ናቸው። ምንሊክ ቴክኖሎጂ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ መላው የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎችን የስራና የማህበራዊ ኑሮ በእጅጉ እንዲያቀላጥፍ በማድረግ፣ በተቃራኒው ደግሞ በወቅቱ ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥርጣሬዎችን በቶሎ ያለመቀበል ተፅዕኖ በብልሀትና በዘዴ ተቋቁመው ቴክኖሎጂን ያስፋፉ መሪ ነበሩ። ባለፉት አምዶች ላይ ከስልክ፣ ባቡር፣ አውሮፕላን እና ቴሌቪዥን ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥ ጋር የተያያዙ ግለሰቦችና ኩነቶችን እንዲሁም አካባቢና ኪነህንጻዎችን ስንዳስስ ቆይተናል። በተመሳሳይ በዚህ አምድ የመኪናን ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥ እንመለከታለን።

አፄ ምንሊክ ኢትዮጵያን ከ1881 ዓ.ም. እስከ 1905 ዓ.ም. በመሩባቸው በ24 ዓመታት በሰፊው ከሚታወቁበት ቅኝ ገዢ ሀይልን ያሸነፉበት የመጀመሪያው የአፍሪካ የአድዋ ድል በተጨማሪ የጣሉት አሻራ ኢትዮጵያን ማዘመናቸው ነው። የአድዋ ድልን ተከትሎ ከአውሮፓውያን ጋር የነበራቸው የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመጠናከሩ በርካታ ምዕራባውያን ወደኢትዮጵያ ንግድ፣ የማዕድን ሀብትና፣ ግብርና በመፈለግ መምጣት ጀመሩ። በዚህም ወቅት ነበር የመጀመሪያዎቹ መኪኖች የአውሮፓ ጎዳናዎች ላይ እየታዩ መጡ።

አጼ ምኒሊክም የአውሮፓውያን የኢንዱስትሪ ውጤቶችና ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ መስፋፋት እንዳለባቸው ቁርጠኛ ስለነበሩ ስልክ፣ ባቡር፣ ባንክ፣ ሰአቶች፣ መሳርያዎች፣ ፖስታ፣ ቴሌግራፍ፣ እና የመሳሰሉ በርካታ፡የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በጥብቅ ክትትልና የበላይ ጠባቂነት በቤተመንግስቱና፡ በአራት ኪሎ አካባቢ በመጀመር አስተዋውቀው ማህበረሰቡ እንዲገለገልባቸው አድርገዋል። ነገር ግን እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ወደአዲስ አበባ በገቡበት ወቅትም ከማህበረሰቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥማቸው ስለነበር የንጉሱ ጥረት እጅግ ተፈትኖ ነበር። ምክንያቱም አንዳንዶቹ እንደ ተፈጥሮኣዊ ያልሆኑ ግዑዝ ነገር ሲቆጥሯቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ የሰይጣን ስራ በማለት ያጣጥሏቸው ስለነበር ነው።

ጊዜው 1900 ዓ.ም. ነበር። ንጉሱ መኪና ከውጭ አገር ማስመጣት እንደሚፈልጉ ለቅርብ ወዳጆቻቸውና አማካሪዎቻቸው አሳወቁ። አውሮፓውያኑም ይህንን ሰምተው ፍላጎታቸውን ቀድመው ለማሟላት አንድ በአንድ ተረባረቡ። ቢዲ ቤንትሊ የተባለ እንግሊዛዊ አጋጣሚውን መጠቀም ቻለ። አርምስትሮንግ ሲድሊ ከተባለ ኩባንያ ጋር በመስማማት፣ አስራ ስምንት የፈረስ ጉልበት ያለው መኪና በጅቡቲ በኩል በመርከብ አስገብቶ ተራራና በረሀውን እያቆራረጠ አዲስ አበባ፡ድረስ ነድቶ አስመጣ።

ቤንትሊ እና ሰራተኞቹ ከኢትዮጵያ ሰራዊት ከተመደበላቸው አጃቢዎች ጋር ሰባት ወራት የፈጀ ጉዞ አድርገው በመጨረሻም አራት ኪሎ ቤተመንግስት ደርሰው ለአፄ ምንሊክ መኪናዋን በስጦታ አበረከቱ። ንጉሱም ከሀር የተሰራውን ጥቁር ካባቸውን ለብሰው እና ትልቁን ባርኔጣ አጥልቀው መኪናዋን ዞረው እየቃኙ ፈተሹና በመዲናዋ በተሰሩት አዲስ መንገዶች ላይ ለመንዳት እንደተዘጋጁ ተናገሩ።

በመጀመሪያ ቤንትሊ ለንጉሱና በቦታው ለማየት ለተሰበሰቡት ሰዎች ሰለመኪናዋ አሰራርና ሁኔታ አጭር ገለፃ ሰጠ። አፄ ምንሊክም በጥሞና አዳመጡትና በአስተርጓሚያቸው ሆህለር አማካኝነት እንዲህ አሉት፣

“አዎ አዎ፣ ይህ ሰው [ቤንትሊን ማለታቸው ነው] እዚህ ድረስ ሊገለኝ ብሎ የመጣ አናርኪስት ግን አይመስልም። ማሽኑም እንደተነገረኝ አደገኛ አይመስልም።” ቀጠሉና “ባለፉት ወራት በየእለቱ በሚባል ሁኔታ ሰዎች መኪናዋ፡ውስጥ እንደተቀመጥኩኝ እንደምፈነዳ እየነገሩ ሊያስጠነቅቁኝ ሲሞክሩ ነበር። እኔም አረ ሞኝነት እንደሆነ ምክንያቱም መኪናዋ ውስጥ የሚነዱትም ፈረንጆች አብርውኝ እንደሚፈነዱ ስነግራቸው፣ መልሰው ‘አይ እነርሱ መጨረሻ ሰአት ላይ ከመኪናዋ ላይ ዘለው መውጣት ስለተለማመዱ እርስዎን ከማፈንዳት ይልቅ ወደ ገደል አፋፍ ነድተው ይገለብጦታል’ አሉኝ” በማለት አጼ ምንሊክ መኪናዋን ላመጡት አውሮፓውያን ስለቴክኖሎጂ ያላቸውን በራስ መተማመን በልበ ሙሉነት አስረዷቸው።

በመኪናዋ ጉዞ ተጀመረ። ለመጀመሪያው ጉዞ ከቤተመንግስት ሁለት ሰዎች አብረው ከምንሊክ ጋር እንዲነዱ ተመረጡና ከግቢ እስከ አራዳ ገበያ ደርሶ መልስ ጉዞ ተጀመረ። ሁለቱ ሰዎች በድንጋጤ ሙሉ ጉዞውን በፍርሀት ተኮማትረው ደረሱ።

አፄው ግን በተቃራኒው ጋቢና ላይ ከሹፌሩ ሬጂናልድ ዌልስ አጠገብ ተቀምጠው በፈገግታ ተጓዙ። የፈረስና፡የእግረኛ አጃቢዎቻቸው እንደተለመደው ቢከተሏቸውም ወዲያው መኪናዋ ጥላቸው ፈረጠጠች። የመኪናዋ ፍጥነት ሲጨምር ንጉሱ እንደወጣትነታቸው በሳቅ እየተፍለቀለቁ ሹፌሩን የበለጠ እንዲፈጥን ነገሩት። ዌልስም እንደታዘዘው አደረገ። ንጉሱም እጅግ ተደሰቱ። አጼ ምንሊክ በ1900 ዓ.ም. በመኪና የተሳፈሩና በኋላም መንጃ ፈቃድ ኖሯቸው የነዱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆኑ።

ተጨማሪ መኪናዎች መምጣትና የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታው ጎን ለጎን መሄድ ስለነበረበት፣ አጼ ምንሊክ ከሶስት አመት ቀደም ብሎ በ1897 ዓ.ም. የመጀመሪያ የመንገድ መዳመጫ ማሽን “steam roller” ሳርኪስ ተርዚያን በተባለ ባለሙያ በኩል አስመጥተው ነበር። በዚህም ማሽን አማካኝነት የመጀመሪያዎቹ የከተማዋ መንገዶች ተጠረጉ። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያም በመዲናዋ ሶስት ዋና ዋና መንገዶች ነበሩ ሲል በወቅቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ የነበረ መራብ የተባለ አውሮፓዊ ጽፏል። የመጀመሪያው የምንሊክ ጎዳና በመባል የሚታወቀው ከዋናው ቤተመንግስት ግቢ አድርጎ በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል በኩል ወደ አራዳ የሚሄደው መንገድ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ መኮንን ጎዳና የሚባለው ከእንጦጦ ጎዳና (ስድስት ኪሎ አደባባይ) በመነሳት በአምስት ኪሎ አርጎ ራስ መኮንን ድልድይን አልፎ ወደ አራዳ ገበያ የሚሄደው ሲሆን፣ ሶስተኛው ጎዳና ከአራዳ ተነስቶ ወደ ደቡብ የምንሊክ ጎዳናን አቋርጦ ፍልውሀ ጋር የሚያልቀው ነበር።

በተጨማሪም ሌሎች ከአራዳ ገበያ ተነስተው ወደየአቅጣጫው የሚሄዱ መጋቢ መንገዶች የነበሩ ሲሆን ለመንገዶች ስራ፡ማዘጋጃ ቤቱ የተለያዩ ስራ ተቋራጮችን በጨረታ ያወዳድር ነበር። ከጋሪ፣ በቅሎና የእግር ጉዞ ጎን ለጎን አዲስ የከተማዋን ትራንስፖርት ምህዳር የተቀላቀሉት መኪናዎችም የመንገድ መሰረተ ልማት አቅርቦት ፍላጎትን እንዲጨምር አደረጉት።

ለማጠቃለል አንድ ማህበረሰብ የቴክኖሎጂ እድገትን በየትኛውም ደረጃ ለማምጣት በመጀመሪያ የባህል ዝግጅት እንደሚያስፈልገው የዘርፉ ታሪክ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ስለሆነም ማንኛውም ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና እዳዲስ አሰራር በማህበራዊና፡የስነልቦና ዝግጅት መደገፍ ይኖርበታል። የአገራት ስልጣኔም ምን ያህል ባህላቸው ከቴክኖሎጂ ለመጠቀምና ለማትረፍ ካለው ዝግጁነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ምሁራኑ ይገልጻሉ። አጼ ምንሊክ በጊዜአቸው በኢትዮጵያ ለአዳዲስ ቴክኖሎጂ ያለው ባህላዊ ቅቡልነት እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በተለይም ቴክኖሎጂዎቹን በአገራችን ለማስፋፋት ጥረት ሲያደርጉ ‘ከሰይጣን ጋር ተዛመዱ’ በመባል የተኮነኑበትን ሁኔታና የማህበረሰቡን አሉታዊ ተጽዕኖ ተቋቁመው ለስልክ፣ ለመኪና፣ ለቲያትር ቤትና ለመሳሰሉት ባህላዊ ቅቡልነት እንዲፈጠር ያደረጉበት ጥበብና ጽናት በኢትዮጵያ ዘመናዊነት ታሪክ ታላቅ የቴክኖሎጂ ወንጌላዊ ያደርጋቸዋል። ቸር እንሰንብት!

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© July, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.