...

The African Building Platform

Updates

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ

Helawi Sewnet Beshah
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

ክፍል1: ስልክ እና ቴሌኮሙኒኬሽን

በኢትዮጵያ አብዛኛው ዘመናዊ የሚባል ቴክኖሎጂ የጀመረውና ወደሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰራጨው ከአዲስ አበባ ነበር። አዲስ አበባ ለአዳዲስ ፈጠራና አሰራሮች፣ ወይም በኢንግሊዘኛው “innovations” በመባል ለሚጠሩት በርካታ መሳሪያዎች መስፋፋትና ቅቡልነት ፋና ወጊ ማዕከል ነበረች፤ አሁንም ሆና ቀጥላለች። በዚህ እና በቀጣይ አምዶች እነዚህ አዳዲስ ፈጠራዎች ወደ ኢትይጵያ እንዲገቡ ከፍተኛ ሚና የነበራቸውን ግለሰቦች እና ከፈጠራዎቹ ጋር የተያያዙትን የአዲስ አበባ ከተማን ሰፈሮች ፣ አካባቢዎች እንዲሁም ኪነህንጻዎች እዳስሳለሁ።

አንድ ማህበረሰብ የቴክኖሎጂ እድገትን በየትኛውም ደረጃ ለማምጣት በመጀመሪያ የባህል ዝግጅት እንደሚያስፈልገው የዘርፉ ታሪክ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ስለሆነም ማንኛውም ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና እዳዲስ አሰራር በማህበራዊና ፣ ስነልቦናዊ ዝግጅት መደገፍ ይኖርበታል። የሀገራት ስልጣኔም ምን ያህል ባህላቸው ከቴክኖሎጂ ለመጠቀምና ለማትረፍ ካለው ዝግጁነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ምሁራኑ ይገልጻሉ። የኢትዮጵያም የዘመናዊነት ጉዞ ከዚህ የተለየ አልነበረም።

የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ጉዞ ለአንድ ክፍለዘመን የቆየውን የዘመነ መሳፍንት አገዛዝ ስርዐት ማክተም ተከትሎ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ይጀመራል። አጼ ቴዎድሮስም ንጉስ ከሆኑ በኃላ ሀገሪቷን ለማዘመን የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን የተለሙ ሲሆን፣ በተለይም በሀገር ውስጥ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለመስራትና ለማምረት ያደረጉት ጥረት በቴክኖሎጂ መዘመን ለነበራቸው ቁርጠኝነት ማሳያ ነበር። ይህንንም ራዕይ ለማሳካት በቁጥጥራቸው ስር የነበሩ አውሮፓውያንን መሳሪያ ማምረት ላይ በግዳጅ እንዲሰማሩ አድርገዋቸዋል።

ነገር ግን የአጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን የማዘመን ቀናዒ ፍላጎት ግቡን ሊመታ አልቻለም። ምክንያቱም በአንድ በኩል ካህናቱ፣ በሌላ ደግሞ የአንዳንድ ክፍለ ሀገር ሀይሎች ተቃውሞ የማይበገሩ እንቅፋቶች ስለሆኑባቸው ነበር። ከምንም በላይ ግን የንጉሱ የዘመናዊ ስልጣኔ ምኞት ፍሬ ያላፈራው ዕሳቤዎቹ ከዘመኑ ልቀው የሄዱ ስለነበርና ተዘርተው የሚያድጉበት ለም አፈር ስላላገኙ እንደሆነ ብዙ የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን ይስማማሉ።
ከአመታት በኃላ አጼ ምንሊክም ተመሳሳይ የዘመናዊ ስልጣኔ ራዕይ ይዘው ይነሳሉ። ንግስናቸውን እና የአዲስ አበባን መቆርቆር ተከትሎ በ19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ በወቅቱ በአለም ዙርያ አሉ የተባሉት የጥበብና፡የፈጠራ መገለጫ አገልግሎቶችና ቁሳቁሶች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ።

በመጀመሪያው ማዕበል ወደከተማዋ የመጡት ባቡር፣ ባንክ፣ ጥይት ፋብሪካ የስልክ መስመር፣ ቴሌግራፍ፣ ወፍጮ፣ በእንፋሎት የሚሄድ ሞተር እና ሌሎችም ሲጠቀሱ፤ በሁለተኛው ዙር ከገቡት የፈጠራ ውጤቶች መካከል ደግሞ ቴያትር ቤት፣ መኪና፣ የቧንቧ ውሀ፣ ሆቴል እና በርካታ ትናንሽ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።

እንደቀድሞው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ወደአዲስ አበባ በገቡበት ወቅትም ከማህበረሰቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥማቸው ነበር። አንዳንዶቹ እንደ ተፈጥሮኣዊ ያልሆኑ ግዑዝ ነገር ሲቆጥሯቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ የሰይጣን ስራ በማለት ያጣጥሏቸው ነበር። ስለሆነም አብዛኞቹ ፈጠራዎች በንጉሱ ጥብቅ ክትትልና የበላይ ጠባቂነት በቤተመንግስቱና፡ በአራት ኪሎ አካባቢ ከማህበረሰቡ ጋር የመጀመሪያ ትውውቃቸውን አድርገዋል። በዚህም አጼ ምኒሊክ የቴክኖሎጂ ባህላዊ ቅቡልነት እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እንደ ልዩ ነገር በጥርጣሬ ይታይ ከነበሩት ቴክኖሎጂዎች መካከል ስልክ ዋነኛው ነበር። የመጀመሪያዎቹን ስልኮች ራስ መኮንን በ1882 ዓ.ም. ከጣልያን እንዳመጧቸው ይነገራል። አራት ኪሎ ቤተመንግስትም ደርሶ፣ አጼ ምንሊክ ከስልክ ጋር ከተዋወቁ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንዱ ይሆናሉ።
በወቅቱ የሰውነት አካል የሌለውን ድምጽ መስማት በአካባቢው ቀሳውስቶች ዘንድ ፍርሀትን የፈጠረና እንደክፉ መንፈስ ስራ የተቆጠረ ስለነበር ስልክ ከቤተክህነት አካባቢ ከፍተኛና የአደባባይ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። በቤተመንግስት ውስጥ ያሉ ቢሮዎችን ለማገናኘት የስልክ መስመር መዘርጋት ሲጀምር ከቤተክርስትያን በተላኩ ቄሶች አማካኝነት የሰይጣን ስራ ስለሆነ መሳሪያው እንዲወገድ የሚል ቅሬታም ቀረበ። ነገር ግን ይህ ለኢትዮጵያ ብቻ ልዩ የሆነ ክስተት አልነበረም። ቴክኖሎጂው በ1868 ዓ.ም. በተፈጠረባት በአሜሪካም ስልክን ከጥንቆላና ፡ ከአስማት ጋር በማያያዝ ሰፊው ማህበረሰብ እስኪጠቀመው ጊዜ ፈጅቷል። ስልክ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ከ14 አመታት በኃላ ወደአዲስ አበባ ስለገባም ምናልባት ኢትዮጵያን በአለም ላይ ከመጀመሪያዎቹ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች ተርታ ውስጥ ይከታታል።

ምንም እንኳን ባህላዊው ተቃውሞ ቢበረታም ለማህበረሰቡ አስተያየት ምላሽ ለመስጠት አጼ ምንሊክ ጳጳሱንና የተከበሩ ግለሰቦችን ቤተመንግስታቸው ይጋብዛሉ። ንጉሱም ከቀሳውስቱ ለደረሰባቸው ተጽዕኖ ያላቸውን ሽረት ከገለጹላቸው በኃላ፣ ተቃውሟቸው የሚቀጥል ከሆነ ኃይማኖታቸውን ወደሌላ እንደሚቀይሩ አስጠነቀቋቸው። እንግዶቹም በመደናገጥ ንጉሱ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩት በመማጸን የስልኩን ቅሬታ እንደሚተዉትና፡ካህናቱም በመንገዳቸው እንደማይቆሙ ቃል ገብተውላቸው ሄዱ ሲሉ የታሪክ መዝገቦች አስፍረዋል።

አጼ ምኒሊክም የስልክን ጥቅም በሚገባ ተገንዝበውት ስለነበር በየኬላው የስልክ ጣቢያዎች ተተከሉ። ከክፍለሀገር ንጉሶችና አስተዳዳሪዎች ጋር በቅርበት ለመገናኘት እና በአገሪቷ ዙርያ ለሚከሰቱ ክስተቶች መረጃ በሙሉና በፍጥነት እንዲደርሳቸው ያደርጉበት ጀመር። ቴክኖሎጂውን መስፋፋት ተቋማዊ ለማድረግ ንጉሱ የፖስታ፣ ስልክና ቴሌግራፍ ሚንስቴር መስሪያቤትን አቋቋሙ። ሳምንታት ይፈጁ የነበሩ ስራዎች በሰዐታት እንዲጠናቀቁ በማስቻል የማዕከላዊው መንግስት እንዲጠናከር ስልክ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበረከተ። ቴክኖሎጂው ከአስተዳደራዊ ፋይዳው ባሻገር የኢትዮጵያ ማህበረሰብን ለማስተሳሰር እና ለማቀራረብ ከፍተኛ ሚናም እየተጫወተ መጣ። ቀስ በቀስም የኢኮኖሚ ፋይዳው እየጨመረ የውጭ ኤምባሲዎችም ሳይቀሩ በክፍያ የስልክ አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ አስችሏል።

የስልክ ቴክኖሎጂ እንደ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት በ1886 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ሀረር ከተማ የመስመር ግንባታን ተከትሎ ተጀመረ። ከ1888 የአድዋ ድል ሶስት አመት በኋላ መስመር ዝርጋታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም ተቃውሞውም ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም እየቀነሰና ቅቡልነቱም እየጨመረ በመምጣት የማህበረሰቡን ቀልብ ሳይቀር የሚገዙ ግጥሞችና ሙዚቃዎች ይሰሙ ጀመር:

“ላኪብኝ በስልኩ ልምጣ በባቡር
የሰው መልክተኛ አጣርቶም አይነግር።
የሰው መልክተኛ ታዛዥ ለምኔ
ላኪብኝ በስልኩ እመጣለሁ እኔ”።

አዝማሪዎች ሳይቀር ንጉሱን በግጥሞቻቸው አወደሱ:

“ባቡሩ ሰገረ ስልኩም ተናገረ
ምኒልክ መላክ ነው መሰለኝ ልቤ ጠረጠረ።”

ከግማሽ ምዕተ አመት በኃላም የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስልጣኔ እውን እየሆነ ለመምጣቱ የስልክ ቴክኖሎጂ አንደኛው ማሳያ ሆነ።

ሳጠቃልል፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስልጣኔ ጉዞ ውስጥ አዲስ አበባ፡ልዩ ሚና ተጫውታለች፣ እየተጫወተችም ትገኛለች። የከተማዋ ስነሕዝባዊ አወቃቀርና ብዝሀነት፣ አጼ ምንሊክ ለቴክኖሎጂ የነበራቸው ራዕይ፣ ጥበብና ቁርጠኝነት፣ የአድዋ ድል ያስከተለው አለም አቀፋዊ እውቅና፣ የውጭ ዜጎችና ነጋዴዎች ወደሀገሪቱ መግባት እና የመሳሰሉት ምክንያቶች ድምር የኢትዮጵያን ዘመናዊ ስልጣኔ አቀላጥፈውታል። በሚቀጥሉት አምዶች የሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደአዲስ አበባ አገባብ እና ስርጭት እዳስሳለሁ። ቸር እንሰንብት!

@HelawiSewnet
helawi.sewnet@gmail.com

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© May, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.