The African Building Platform

Trending

አዲስ አበባ እና አድዋ

ህላዊ ሰውነት በሻህ (አርኪቴክት)
Helawi Sewnet Beshah (Architect)
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

አንድ መቶ ሃያ አምስተኛውን የአድዋ ድል በምንዘክርበት በዚህ የካቲት ወር በዚህ መጣጥፍ መመልከት የምፈልገው ታሪካዊው የአድዋ ድል፣ የኢትዮጵያ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ አሁን ለያዘችው ማንነት እና ዘርፈ ብዙ የእድገት ደረጃ ያደረገውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለመዘከር ነው።

አዲስ አበባ በ 1878 ዓ.ም. በንግስት ጣይቱ አማካኝነት እንደተቆረቆረች የታሪክ ማህደራት ያስታውቃሉ። ከተማዋ የተመሰረተችው የሸዋ ክፍለ ሀገር ንጉስ የነበሩት አጼ ምንሊክና ባለቤታቸው ንግስት ጣይቱ ከተማ የማቋቋም የረጅም ጊዜ ዕቅድ ኖሯቸው ሳይሆን፣ በወቅቱ በነበረው ተንቀሳቃሽ የሆነ የአሰፋፈርና የአከታተም ባህል ምክንያት፣ እንደ ጊዜያዊ ወታደራዊ ካምፕነት እንድታገለግል ፈልገው እንደነበር ብዙ ምንጮች ይጠቅሳሉ። በዚህ ሁኔታ ባልተጠበቀ ክስተት በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት አጼ ዮሐንስ በጦርነት ይገደሉና፣ አጼ ምንሊክም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሆነው ይሰየማሉ። አዲስ አበባም ባልተጠበቀ ሁኔታ ከተቆረቆረች በሶስተኛ አመቷ የማዕከላዊው መንግስት መቀመጫና የአገሪቷ መዲና ለመሆን ትበቃለች። በተጨማሪም ይህ የአዲስ አበባ ጥንታዊ አሰፋፈር በሳይንሳዊ አጠራሩ መሪ ፕላን ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን፣ በኢትዮጵያውያን ጠንሳሽነት፣ ዕሳቤ እና ዕቅድ ተቃኝቶ ስለተነደፈ፣ ከተማዋ በአፍሪካ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ካሉ ትላልቅ ከተሞች የተለየችና የራሷ የሆነ ልዩ ባህሪያት እንዲኖራት እንዳስቻለ የተለያዩ ምሁራን ይገልጻሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአውሮፓ ሀያላን መንግስታት በጀርመኗ ከተማ በርሊን በመሰባሰብ “ስክራምብል ፎር አፍሪካ” በመባል የሚታወቀውን ኮንፈረንስ ያካሄዱበት እና ወራት የቆየ ምክክር በማድረግ፣ የአፍሪካን መልከአምድር ከታትፈው የተመዳደቡበት እንዲሁም ቅኝ ለመግዛት አህጉሪቷን የወረሩበት ወቅት ነበር። በዚህ ክፍፍልም ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛቱ ስልቻ ውስጥ ትወድቅና በጥንታዊቷ የአውሮፓ ሀገር ጣልያን ሉአላዊነቷ እና ዳር ድንበሯ ይደፈራል።

የሀገርን ድንበር መከላከል አማራጭ የማይሰጠው የማንኛውም መንግስት ሀላፊነትና ግዴታ በመሆኑ ንጉሰ ነገስቱ የክተት አዋጅ ከአዲስ አበባ ያሰማሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ጀግና ልጆችም ከየአቅጣጫው ወደሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በመዝመት በአድዋ ተራሮች ላይ የጣሊያን ጦርን ድባቅ መተው ድል ይጎናጸፋሉ፤ አገራቸውንም ከቅኝ ግዛት ቀንበር በደምና በአጥንታቸው ይታደጋሉ። ይህ የአድዋ ድልም በዓለም ታሪክ፣ ጥቁር ህዝቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓን ሀያል ጦር ድል የመቱበት ተምሳሌትና በቀጣይም በአለም አቀፍ ደረጃ ለመጡ የነጻነት ትግሎች ትልቅ መሰረት እና ተስፋ የጣለ ታሪካዊ ክስተት ይሆናል። በድሉ ማግስትም በወቅቱ የአለም ሀያላን የተባሉት ሀገረ መንግስታት፣ እንግሊዝ፣ ሩስያ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ እንዲሁም ኢትዮጵያ ላይ ወረራ አድርጋ ቅኝ ልትገዛት የነበረችው ጣሊያንም ሳትቀር፣ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት እውቅና በመስጠት አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሚስዮኖቻቸውን ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ በመላክ ኤምባሲዎቻቸውን መክፈት ይጀምራሉ።

ይህንንም ተከትሎ የውጭ አገር ዜጎች ከየሀገሩ ወደአዲስ አበባ ይፈልሳሉ። በተለያዩ የልማት፣ የግንባታ እና የንግድ ስራዎች በመሰማራትም ለከተማዋ እድገት እንዲሁም ቅርጽና ይዘት ቀላል የማይባል አስተዋጽዖ ያበረክታሉ። ወደ መዲናዋ ከገቡት ዋና ዋና ከሚባሉት የውጭ ማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ግሪኮች፤ አረቦች፣ ህንዶች እና አርመኖች የአንበሳ ድርሻውን ይይዛሉ።

ግሪኮቹ በድንጋይ ካባ፣ በመጠጥ ንግድ፣ በጫማ ስራ፣ የቴሌግራፍ ቢሮ ውስጥ፣ በኪነ ሕንጻ፣ በግሮሰሪ፣ ካፌ፣ ሬስቶራንት፣ ጸጉር ቤት እና ልብስ ስፌት የተሰማሩ ሲሆን፣አረቦቹ ደግሞ በአብዛኛው በእጣን ኤክስፖርትና በግመል ትራንስፖርት እንዲሁም የቁራንና የተለያዩ ሀይማኖታዊ ቁሶች ንግድ ላይ ተሰማርተው ነበር። በተመሳሳይ ህንዶቹ፣በግንባታ፣ በቅርጻቅርጽ፣ በልብስ ስፌት፣ ጸጉር ቤትና የወርቅና የብር ሙያ ስራዎች ላይ ይሰማሩ የነበር ሲሆን፣አርመኖቹ ደግሞ በወርቅ ስራ፣ በመጠጥ ንግድ እንዲሁም በቤተመንግስት ውስጥ በምህንድስናና በተለያዩ የሜካኒክ ሙያን የሚጠይቁ ቁሳ ቁሶች ጥገና ላይ ጥበባቸውን አሳርፈዋል። በተጨማሪም የተማረኩት የጣልያን ወታደሮች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ይደረግና የተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል። የአዲስ አበባ ዕድል ፈንታ እንዳይቀየር ሆኖ መሰረት ይተክላል።

ከተማዋ ከተመሰረተች አስራ ስምንት አመት እንዳስቆጠረች፣ ምዕራባውያኑ የከረመ ልማድ አይለቅ እንደዘበት እንደሚሉት የአድዋ ድል ከተከሰተ አስር አመት ሳይሞላ፣ ምንሊክ ሌላ ቦታ ለመስፈር እና ለአስተዳደራቸው አዲስ ከተማን ለመቆርቆር በማሰብ ቤተመንግስት ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አዲስ አለም ላይ ያስገነባሉ። ነገር ግን ይህን የንጉሱን ሀሳብ ልብ ያላሉት አንድ ከባድ ተግዳሮት ይገጥመዋል። ለካ አጼ ምንሊክ የዘነጉት አዲስ አበባ ከሃያ አመት በፊት ሲመሰርቷት የሚያውቋት ትንሽዬ መንደር ሳትሆን፣ አሁን በአገሪቷ ከሚገኙት ትልልቅ ከተሞች ተርታ የተሰለፈች፣የተለያዩ ሰፈሮች ለምተውባት ብዙ ኢትዮጵያውያንን እና የውጭ አገር ዜጎችን የምታኖር፣ እንዲሁም በርካታ የሚባሉ የንግድ ቤቶችን የያዘችን የአገሪቷ ኢኮኖሚ የሚዘዋወርባት ትልቋ ቀጠና መሆኗን ነበር።

ይህም ጉዳይ እየተበራከተ በመጣውና በተለያዩ የንግድ እና የማህበራዊ አገልግሎት ስራ መስኮች ላይ በተሰማራው የከተማዋ ነዋሪ ዘንድ ይሰማና፣ በአብዛኛው ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎችና ከውጭ ሀገራት በመምጣት ሀብትና ንብረት አፍርቶ እየኖረ የነበረው የአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ ቅሬታ ይፈጥራል። እንደሚጠበቀውም ቅሬታው ወደ ንጉሱ ጆሮ ሳይደርስ አልቀረምና፣ አጼ ምንሊክ ወደ አዲስ አለም መናገሻቸውን የማዘዋወር ሀሳባቸውን እንደተዉት በታሪክ ምሁራን ይነገራል።

ለመጨረሻ ጊዜም አዲስ አበባ የአገሪቱ ዋና ከተማ ሆና የመቀጠል ፈተናዋን ታልፍና፣ ከግማሽ ምዕተ አመት በኋላ፣የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ዋና መዲና ለመሆን ያበቃትን የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷን እንድትጎናጸፍ ያ የአድዋ ድል ትልቅ መሰረት ጥሎ አልፏል።

ለዚህም ነው የአድዋ ድል ባይከሰት እና በድሉ ማግስት የአዲስ አበባ ስነሕዝባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቅንብር አገራዊና አለም አቀፋዊ ይዘት ባይዝ፣ በተጨማሪም ይህን ተከትሎ አዲስ አበባ ፈጣን የሆነ የከተማ እድገት ባታስተናግድ ኖሮ፣ ንጉሰ ነገስቱ ሌላ ከተማ፡ ሂደው የመስፈር እድላቸው ከፍተኛ ይሆን ነበር፤ አዲስ አበባም አሁን ላለችበት ትሩፋትና ማንነት ላትበቃ ትችል ነበር፤እንዲሁም የአድዋ ድል ለአዲስ አበባ አሁናዊ ማንነት የማይተካ አሻራውን ጥሎ ሄዷል የምለው። እንግዲህ ምን ይባላል? ውለታ መላሽ ያድርጋት ነው እንጂ!

@HelawiSewnet Helawi.sewnet@gmail.com

Spotlight

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© May, 2023 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.