...

The African Building Platform

Updates

መርኀ ሠናይ

ውሂብ ከበደ
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

አህሰዓ ወረዳ በዓድዋ አውራጃ ሰሜናዊ ጫፍ የሚገኝና መንገድ ያልገባበት አካባቢ በመሆኑ የወረዳው ገዢ ሥራቸውን ለማከናወን ያለባቸውን ችግር ለአውራጃው ገዢ ሲያመለክቱ የአስተዳደር ሥራ ለማከናወን እንኳን መቀመጫ ቦታ እንደሌላቸው ገልጸው ኖሮ የወረዳው ከተማ የሚሆነውን ቦታ ለመምረጥና ለመቀየስ ትዕዛዝ ደረሰኝ። የወረዳው ገዢ ቆፍጣና እና ታታሪ ስለነበሩ አውራጃ ገዢው ደጃዝማች ኃይለ ሥላሤ ገብረ መድህን ቦታው ሲመረጥ እንዲገኙላቸው በመጠየቃቸው አንድ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ወረዳው ተንቀሳቀሰ። እኔም ሜትሬንና ሬንጅ ፖሎቼን ይዤ ከቡድኑ ጋር በመኪና ወደ አዲግራት በሚወስደው መንገድ ተጓዝኩ፡፡ ሃያ ኪሎሜትር ያህል ከተጓዝን በኋላ አንድ ግዙፍ የፈረሰ ቤት አጠገብ እንደደረስን ከመኪና ወርደን የፈረሰውን ቤት ዙሪያ እያየን ጥቂት ስለቆየን ከተባለው ሥፍራው የደረስን መስሎኝ ነበር። ግን ለዓድዋ ቅርብ በመሆኑና መንገድም ስላለ ግር ብሎኛል። ጣሊያን የገነባው የመሰለኝን የፈረሰ ቤትም እየዞሩ ለምን እንደሚያዩ ግልጽ አልሆነልኝም። ጥቂት እንደቆየን በቅሎዎች ቀረቡና ጉዞ ወደሰሜን አቅጣጫ ቀጠልን። በኋላ እንደተረዳሁት የፈረሰ የጣሊያን ግንባታ የመሰለኝ ታሪካዊው የየሃ ቤተመቅደስ ነበር።

የበቅሎ ጉዟችን ረጅምና አድካሚ ቢሆንም አልፎ አልፎ የገጠር የልጃገረዶች የአውራጃ ገዢውን ስም እያወደሱ በመዝፈን እያዝናኑን አመሻሹ ላይ ከምናድርበት መንደር ደረስን። በበነጋታው ተነስተን ቡድኑና ከአካባቢው መንደሮች የመጣው በርካታ ሰው በአቅራቢያው ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያን አመራ። የቤተ ክርስቲያኑ ሥነ ሥርዓት እንደተጠናቀቀ በአንድ ገላጣ ቦታ ላይ የወረዳው ገዢ ለወረዳው ዋና ከተማነት ስለታሰቡት ሁለት አማራጭ ቦታዎች ገለጻ ካደረጉ በኋላ ከተሰበሰቡት ሰዎች መሃልም አንዳንዶቹ አስተያየት ሰጡ። በዚየን ጊዜ ትግሪኛ አጥርቼ ስማልሰማ የተነገረውን በቅጡ ባልረዳም ከሁለቱ ቦታዎች አንደኛው እንዲመረጥላቸው አጥብቀው የሚፈልጉ ሁለት ቡድኖች እንዳሉ ጠርጥሬያለሁ። ቦታዎቹ እጅግም የተራራቁ ስላልነበሩ የተሰበሰበው ሰው በሙሉ ቦታዎቹን በየተራ ለማየት ተንቀሳቀሰ። በቦታዎቹ ስንደረስም ገለጻ የሚያደርጉ ሰዎች ነበሩ። ሁለቱ ቦታዎች ከታዩ በኋላ አውራጃ ገዢው ወደኔ ዞር አሉና የትኛው ቦታ እንደሚሻል አስተያየት እንድሰጥ ጠየቁኝ። ያልጠበቅኩት ስለነበር መደናገጥ ቢሰማኝም ሃሳቤን ሰብሰብ አድርጌ በመጨረሻ ያየነውና አሁን የምንገኝበት ቦታ እንደሚሻል ፈርጠም ብዬ ተናገርኩ። በዚያን ጊዜ ይህኛው ቦታ እንዲመረጥ የሚፈልጉት እንደተደሰቱና ሌላኛው ቦታ እንዲመረጥ የሚፈልጉት ደግሞ እንዳዘኑ ተመለከትኩ። መቼም እኔ አስተያየት ሰጠሁ እንጂ ወሳኝ ስላልሆንኩ አይቀየሙኝም ብዬ እያሰብኩ እያለ አውራጃ ገዢው ምክንያቴን እንድገልጽ ጠየቁኝ። የመጀመሪያው ቦታ ወጣ ገባና ገላጣ ከመሆኑም በላይ ባቅራቢያው ውሃ የለም፤ ይህኛው ግን ባብዛኛው ደልዳላና በመጠኑም ቢሆን የዕጽዋት ሽፋን ያለውና በአቅራቢያውም ወንዝ እንዳለ አስረዳሁ።

አውራጃ ገዢውና በዙሪያቸው የነበሩት ሰዎች ጥቂት ከተመካከሩ በኋላ ለተሰበሰበው ሕዝብ መሐንዲሱ ባቀረበው አስተያየት መሠረት አሁን ያለንበት ቦታ የወረዳው ዋና ከተማ እንዲሆን መወሰኑ ተገለጸ። ወዲያው በውሳኔው የተደሰቱት ሰዎች ለአውራጃ ገዢው አሁኑኑ ይቀየስልን ብለው አመለከቱና ተፈቅዶላቸው እኔም ሥራ እንድጀምር ታዘዝኩ። ያልጠበቅኩት ቢሆንም ዙሪያውን ከቦ የሚያየኝ ሕዝብ እንደቲያትር እየተመለከተኝ ሬንጅ ፖሌን እየተከልኩና እየነቀልሁ እላይና ታች እያልኩ ሥራዬን ቀጠልኩ። መጀመሪያ በደልዳላው ቦታ መሃል ከሰሜን ወደ ደቡብ የከተማውን ዋና መንገድ ተገቢውን ስፋት ሰጥቼ ቀየስኩ። ከዚያም የከተማው የገበያ ቦታ የሚሆነውን ከልዬ ችካል አስመታሁ። ቀጥሎም ሌሎች መንገዶችን አወጣሁ። ለትምህርት ቤት፤ ለጤና ጣቢያ፤ ለአስተዳደር ጽሕፈት ቤትና ለፖሊስ ጣቢያ ቦታዎችን መደብኩ። ትኩረቴ በሙሉ ሥራው ላይ ስለነበር ድካም አልተሰማኝም ነበር። በመሀሉ አንድ ሰው ጠጋ አሉኝና፤ አለቅን እኮ፤ ቁርስ አላደረግንም የምሳ ሰዓትም አለፈ ዘጠኝ ሰዓት ሊሆን ነው አሉኝ። ደግነቱ ያሰብኩትን ፈጽሜ ስለነበር ለአውራጃ ገዢው አስታውቄ በተለይ የቦታ ምደባውን እየዞርን አሳየሁ።

አሁኑኑ ይቀየስልን ያሉት ሰዎች አሁን ደግሞ ወደ አውራጃ ገዢው ቀርበው ሌላ ጥያቄ አነሱ። ይኸውም የከተማው ወሰን ተለይቶ ይታወቅልን የሚል ነበር። እዚህም ላይ አስተያየት ተጠይቄ በጽሑፍ እንጂ በቅየሳ ሊሆን እንደማይችል በማሳሰቤ መለያ ምልክቶቹን በመለየት እንድወስን ተጠየቅኩ። ጉብታዎችን፤ ተረተሮችን፤ ዛፎችን እና የመሳሰሉትን በተለይም በስተምዕራብ ያለውን ወንዝ በመጥቀስ ሰፋ ያለ የከተማ ክልል ወሰንኩ። ዛፍን በሚመለከት በጊዜው ከባህር ዛፍና ከጽድ ሌላ የዛፍ ስም ስለማላውቅ … በትግሪኛ ሞሞና ከሚባለው ዛፍ ተነስቶ እስከ … ድረስ… ቀጥሎም… እየተባለ እንደተጻፈ ትዝ ይለኛል።

የከተማው ክልል እዚየው ተጽፎ ካለቀ በኋላ ሊፈረም ሲል ሌላ ጉዳይ ተነሳ። ከተማው ስም ይውጣለት ተባለና አማራጮች ቀረቡ። እዚህ ላይ አስተያየት አልተጠየቅሁም። ከቀረቡት አማራጮች ግን እኔ በልቤ የወድደኩት ተመረጠ። ከተማውን መርኀ ሠናይ ብለነዋል ተባለ። ሕዝቡም ባብዛኛው ደስታውን ገልጾ ወደ ተዘጋጀው የግብዣ ቦታ አመራ። እንደዚያ ባለ ገጠር ውስጥ ይዘጋጃል ብዬ ያልጠበቅሁት ዓይነት ግብዣ ቀርቦ እስከ ምሽቱ ድረስ ቀጠለ። በበነጋታውም በመጣንበት አኳኋን ወደ ዓድዋ የመልስ ጉዞ ሆነ።

የአርኪቴክቸርና የከተማ ፕላን አነሳስ የትምህርት ክፍል፤ የከተማ ፕላን አነሳስ ኮርሶችን የሚሰጠው ከአራተኛ ዓመት ሁለተኛ ሴሚስተር ጀምሮ ነው። የመጀመሪያው ኮርስ የከተማ ፕላን አነሳስ ታሪክን የሚመለከት ሲሆን ዋነኞቹ ሁለት ኮርሶች ግን የሚሰጡት አምስተኛ ዓመት ላይ ነው። ከሦስት ዓመት በኋላ እንደ ኮርስ ሥራ የሻሸመኔን ከተማ ፕላን ከጓደኞቼ ጋር በምንሠራበት ጊዜ በሃሳብ ወደኋላ እየተመለስኩ መርኀ ሠናይን አስብ ነበር። ከሃያ ዓመት በኋላ ደግሞ በኢጣልያ መንግሥት ትብብር የተዘጋጀው ማስተር ፕላን በዓዋጅ በሚጸድቅበት ወቅት አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እሠራ ስለነበር የከተማው ክልል በጽሑፍ ጭምር እንዲሰፍር አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ። እንደ መርኀ ሠናይ ሁሉ … የፋንታን ወንዝ ተከትሎ … እስከሚገናኝበት ድረስ … እየተባለ እንደተጻፈ ትዝ ይለኛል።

በካርታ ላይ N 14º 21´ E38°58´ ን ይዛ የምትገኘውን መርኀ ሠናይ በ Google Earth ስመለከታት ከሞላ ጎደል ያወጣኋቸው መንገዶችና የመደብኳቸው ቦታዎች ቁልጭ ብለው ይታዩኛል። የከተማዋ ዕድሜ ከሃምሳ ዓመት በላይ እንደመሆኑ እድገት አሳይታለች። ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ክረምት ከበጋ የሚያገናኛት የመኪና መንገድ ያለ ባይመስልም ሌሎች የልማት ሥራዎች ተሰርተዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የስፖርት ሜዳና የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች በአየር ካርታው ላይ ይታያሉ። በካርታዎች ላይ የወረዳው ስም አህሰዓ እንጂ የከተማው ስም ተጽፎ ስለማይታይ ለወደፊት ለካርታ አዘጋጆችም ሆነ ለአስተዳደር አካላት ይህ ጽሑፍ ማስታወሻ ሊሆን ይችላል።

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© October, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.