...

The African Building Platform

Updates

ምርጫና የማገጃ ግንብ

Wouhib Kebede
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

በብዙ ረገድ ከአክሱም ይልቅ በዓድዋ የነበረኝ ማኅበራዊ ሕይወት ቢያመዝንም፤ ግማሹን የአገልግሎት ጊዜ አክሱም በማሳለፌ ተመሳሳይ ሥራ አከናውኛለሁ። ለየት ብሎ ያገኘሁት ግን ከ1961 የምርጫ ዘመን ጋር በተያያዘ ባከናወንኩት የግምት ሥራ ወቅት ያጋጠመኝ ልዩነት ነበር። በምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመመዝገብ አንድ ሰው ቢያንስ 1500 ብር የሚገመት ንብረት ባለቤት መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። ይህን ማረጋገጫ በሁለቱም ከተሞች የምሰጠው እኔ ነበርኩ። በዚያን ጊዜ የአንድ የፓርላማ አባል ደምወዝ 700 ብር እንደነበረ ሰምቼ ስለነበር ብዙ ዕጩዎች ንብረታቸውን ለማስገመት በብዛት መጠየቃቸው ብዙም አላስገረመኝም።

አነስተኛም ብትሆን ቤትና ቦታ ይገመትልኝ ብሎ የቀረበን ሰው ከ1500 ብር በታች ገምቼ የማሳዝንበት ምክንያት አልታየኝም። አክሱም ውስጥ የግምት ቀጠሮ ያስያዙ ዕጩዎችን ንብረት ለመገመት ወደቦታቸው ለመሄድ ስንቀሳቀስ ግን ጭቃ ሹሞቹና ሜትር የሚይዙት ረዳቶች በድንገት እየተሰወሩብኝ ግራ አጋብተውኝ ነበር። ቆይቶ ግን ምሥጢሩን ከሌሎች የከተማው ነዋሪዎች ጠይቄ በመረዳቴ የትኛውንም ወገን የማያስቀይም መፍትሄ አግኝቼለት ያመለከቱት ዕጩዎች በሙሉ መወዳደር እንዲችሉ አደረግሁ።

ዓድዋ ውስጥ የነበረው የምርጫ ሁኔታ ሞቅ ያለ ነበር። ሊያሸንፍ ይችላል ተብሎ በአብዛኛው ነዋሪ የታመነው ሰውም (Front Runner) ይታወቅ ነበር። ቅስቀሳ የሚካሄደውም በበራሪ ወረቀት፤ ፖስተር በመለጠፍ ወይም በድምጽ ማጉያ በመለፈፍ ሊሆን የሚችልበት ዘመን አልነበረም። ደጋፊዎች፤ በአብዛኛው ሴቶች፤ በየአካባቢው ሰብሰብ ብለው በሚያሰሙት ዘፈን የሚደግፉትን ዕጩ እያወደሱ እግረ መንገዳቸውን አላፊ አግዳሚውን ያዝናኑ ነበር ፤ ከማስታውሳቸው የዘፈን ስንኞች የሚቀጠለው ይገኝበታል።

እምባባ ዕረ፤ እምባባ ዕረ
እታ ምርጫ ወሲዱዋ ሠይፉ ታፈረ

የአቶ ሠይፉ ታፈረ ተወካዮች 60x60x60 ሳ.ሜ. የሆነችው የምርጫ ሳጥን ከየወረዳው በበቅሎ ተጭና ወደ ዓድዋ የቆጠራ ጣቢያ ስትላክ ከፖሊሶች ጋር አጅበው ሲያመጡ አይቼ ትጋታቸው ይገርመኝ ነበር። ጥረታቸው ውጤት አግኝቶ፤ ዘፈኑም ሰምሮ፤ እውነትም አቶ ሠይፉ ታፈረ የ1961ን የፓርላማ ምርጫ በማሸነፍ የዓድዋ አውራጃ ሕዝብ እንደራሴ ሆነው ፓርላማ ገቡ።

የምርጫ ጉዳይ ከተጠናቀቀ በኋላ ሞቅ ብሎ የነበረው የዓድዋ ከተማ ድባብ ወደነበረበት በመመለሱና ክረምትም እየገባ ስለነበር መነጋገሪያ የሚሆን ጉዳይ አልነበረም፡፡ አንድ ቀን ዝናብ አርፍዶ ጀምሮ ሳያቋርጥ እየዘነበ ስለነበር በጊዜ ወደ ቤቴ ገብቼ እያለሁ ከምሽቱ ሁለት ሠዓት አካባቢ ሰዎች በጥብቅ ትፈለጋለህ ብለው ቤቴ ድረስ መጡ። ማነው የሚፈልገኝ ብላቸው፤ አቶ ወልደገብርኤል የአሰም ሆቴል ባለቤት ናቸው ስላሉኝ ተያይዘን ወደ ቦታው ሄድን።

እዚያ ስደርስ የአሰም ወንዝ ድልድይ ላይ ብዙ ሰው ተሰብስቦ ከታች እየጋለበ የሚመጣውን ከባድ ጎርፍ ይመለከታል። ሆቴሉ ከድልድዩ አጠገብ ሆኖ መታጠፊያ ላይ ስለሆነ የጎርፉ ውሃ በድልድዩ ስር ከማለፉ በፊት የሆቴሉ ድንበር ላይ የተገነባውን የማገጃ ግንብ በሙሉ ኃይሉ ያላጋው ነበር። የተሰበሰበው ሕዝብ፤ ጎርፉ ከአሁን አሁን የማገጃ ግንቡን ደርምሶ በከፊል ከላዩ ላይ የተጀመረውን ቤት ጭምር ይንዳል ብሎ ኃሳብ ውስጥ ገብቶ ይመለከታል። እኔም ስመለከተው እጅግ ያስፈራ ነበር። እህ ምን ይመስልሀል አሉኝ። በዚያ አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ምን ማለት እንዳለብኝ ማሰብ አሰቸጋሪ ነው። መጀመሪያ ስለሁኔታው መግለጫ መስጠት አለብኝ ቀጥሎም ስለሚከተለው ውጤት ማስረዳት ይጠበቅብኛል። ሁሉም ሰው አትኩሮ ይመለከተኛል። ትርኢቱን ጥቂት ደቂቃዎች ከተመለከትኩ በኋላ አንድ ነገር ትኩረቴን ሳበው። የጎርፉ ውሃ በማገጃው ግንብ አናት ላይ እየዘለለ ወደ ሆቴሉ ግቢ ይገባል። ፊት ለፊት ግንቡን ከሚመታው ጋር ተዳምሮ ወደ ግቢው የገባው ውሃ የመደርመሱን ጉዳይ ያፋጥናል ብዬ አሰብኩ። መደርመሱ አይቀርም የሚል ቃል ለተሰበሰበው ሰው መናገር ግን ከበደኝ። ጥቂት ደቂቃዎች እያየሁ ከቆየሁ በኋላ ልብ ሳልለው ቆይቼ የነበረ ጉዳይ ተመለከትኩ። ይኸውም ግንቡን የሚያላጋው ውሃ ወጣ ወረድ በሚልበት ቅጽበት ከግንቡ በላይ ዘልሎ ግቢው ውስጥ የተጠራቀመው ውሃ በማስተንፈሻ ፉካዎች (Weep holes) በኩል ተመልሶ ወደ ወንዙ ሲገባ አየሁ። የማቀርበው ምክንያት አገኘሁ። አይደረመስም ለማለት የሚያስችለኝ። ምክንያቱንና ድምዳሜዬን ስገልጽ ተሰብስቦ የነበረው ሰው የእፎይታ ስሜት ይታይበት ነበር። እምነትም አድሮበታል። ለማንኛውም ግማሽ ሰዓት ያህል ቆይቶ ወደየቤቱ ሲሄድ እኔም ቤቴ ገባሁ። ባደረበት እምነት ምክንያት ተሰብስቦ የነበረው ሰው መቼም መልካም እንቅልፍ ተኝቶ አድሯል። እኔ ግን ጠዋት ስነሳ ተደርምሶ ቢገኝ ምን እላለሁ በሚል ስገላበጥ እንቅልፍ አጥቼ አደርኩ።

በ 2009 የተነሳ የማገጃው ግንብ ፎቶግራፍ ይኸውና፡፡ የማስተንፈሻ ፉካዎቹ (Weep holes) የዚያን ጊዜ ተለቅ ያሉና የተቀራረቡ እንዲሁም በአንድ መስመር ብቻ የነበሩ ይመስል ነበር፡፡ በአየር ለውጥ ምክንያት የአሰም ወንዝ ክረምት ላይ ኃይል ጨምሮ የሚያላጋ አይመስልም፡፡ የማገጃ ግንቡም ለሌላ 50 ዓመት አገልግሎቱን ሳይቀጥል አይቀርም፡፡

በሚቀጥለው ቀን በድልድዩ በኩል ሳልፍ የወንዙ ውሃ ጎድሎ ሠላም ሆኗል። ጉዳዬ ብሎ ዘወር ብሎ የሚመለከተውም የለም። እኔ ግን የዓድዋ ማዘጋጃ ቤት ሹም በጠየቁኝ መሠረት ከሰኔ 30 በኋላ መደበኛ ተልዕኮዬ አልቆ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ቢኖረብኝም ጥያቄውን ተቀብዬ ክረምቱን ዓድዋ ውስጥ ብቻ ለመሥራት ተስማምቼ ነበር። እስከ መስከረም ይህ የማገጃ ግንብ አንድ ነገር ቢደርስበት መፍትሔ ፈልግ መባሌ አይቀርም። በድልድዩ በኩል በየቀኑ ማለፍ አብዛኛው ሰው የሚፈጽመው ተግባር ቢሆንም እኔ በተጨማሪ አንገቴን መለስ በማድረግ ግንቡ ደህና ውሎ ማደሩን መመልከት የዘወትር ተግባሬ ሆነ። ሐምሌ 22 ቀን 1961 ዓ.ም 20ኛ የልደት በዓሌን ሳከብርም ለማስታወሻ እንዲሆነኝ፤ በርሔ መሊጥ ከሚቀመጥበት አግድም ትይዩ ባለው የድልድዩ መከለያ ግንብ ላይ ተቀምጬ፤ የማገጃ ግንቡ ከኋላዬ በሚታይበት አኳኋን ፎቶግራፍ ተነሳሁ። የዚያን ጊዜ በማገጃ ግንቡ አናት ላይ ተጀምሮ የነበረው ባለ ሁለት ፎቅ አልቤርጎ አልቆ ሥራ ጀምሮ ነበር። በማገጃ ግንቡ ላይ ተጨማሪ ጭነት ሲታከልበት ግን ያማከረኝ አልነበረም።

በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ዓድዋ እና አክሱም ከመመደቤ በፊት አራት ኪሎ በነበረው የኢንጂኒየሪንግ ኮሌጅ በነበረኝ ቆይታ በትምህርቴ ላይ እምብዛም የማላተኩር፤ ወደ ጨዋታ የማዘነብል፤ ካፊቴሪያ ውስጥ ቴሌቢዥን እስኪከፈት ጠብቄ እስኪዘጋ ድረስ በመቆየት ወደ መኝታ ክፍሌ መሄድ የማዘወትር ነበርኩ። የትምህርት ውጤቴም ዝቅተኛ ነበር። ቀደም ብሎም በሁለተኛ ደረጃና በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የነበረኝ ቆይታ ተመሳሳይ ነበር። አገር ዓቀፍ ፈተናዎችን ግን በተሻለ ውጤት ማለፍ የቻልኩት የተማርኩባቸው ትምህርት ቤቶች ደረጃ ከሌሎች ትምህርት ቤቶች የተሻለ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም።

አግለግሎቴን ጨርሼ የሦስተኛ ዓመት ትምህርቴን ለመጀመር ስመለስ፤ ከአራት ኪሎ ወደ አምስት ኪሎ ይዛወራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የአርኪቴክቸር የትምህርት ክፍል፤ በወቅቱ የነበሩት የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ፤ ትውልደ-ቼክ አሜሪካዊው ዣን ራይነር አመቺ ነው ብለው ወዳሰቡት ወደ ሕንፃ ኮሌጅ ተዛውሮ ጠበቀኝ። እኔም አመቺውን ሁኔታ በመጠቀም በትምህርቴ ላይ የማተኩርና ከቴሌቪዥን አዳራሽ ይልቅ መፃሕፍት ቤት አዘውታሪ ሆንኩ። የትምህርት ውጤቴም በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሻለ። አሁን ላይ መለስ ብዬ ሳየው በሙያ ረገድ የቀረጸኝ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ቆይታዬ እንደሆነ ይሰማኛል።

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© October, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.