...

The African Building Platform

Updates

ሥራ እና አገልግሎት

ከ ውሂብ ከበደ
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

በመጀመሪያ የደረስኩት ዓድዋ ስለነበር ቀድመውኝ ደርሰው ቤት ተከራይተው ከነበሩ ንግሥተ ሳባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምኅርነት ከተመደቡ አራት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ተሳታፊዎች ጋር ተዳበልኩ። የአክሱም ሥራዬን በየአሥራ አምስት ቀን እየተመላለስኩና ሆቴል እየተቀመጥኩ ቀጠልኩ። የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ተሳታፊ ደምወዝ ብር 175 ቢሆንም የአንድ ወር ደምወዝ በቅድሚያ አዲስ አበባ እያለ ስለሚሰጥ በየወሩ ብር 157.50 ብቻ ይደርሰዋል። በወቅቱ የኑሮ ሁኔታ አዝናንቶ የሚያኖር ነበር።

የሁሉም ተሳታፊ ዓላማ የተመደበበትን የአስር ወር ጊዜ በሚገባ አከናውኖ ወደ ሚቀጥለው ዓመት ትምህርቱ መመለስ ብቻ ነበር። በመምኅርነት የተመደቡት ሥራቸው መመሪያ ያለውና በተወሰነ መንገድም የተደጋጋሚነት ፀባይ ያለው ነው። እኔ የተመደብኩበት ማዘጋጃ ቤት ግን ይህ ነው የሚባል አሰራር የሌለውና በየቀኑ በሚከሰቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። በመጀመሪያ አካባቢ የሚመጣ ባለጉዳይም ሆነ የበላይ ትዕዛዝ ባለመኖሩ ቀኑን ሙሉ አሮጌ ማኅደሮችን ከማገላበጥ በቀር ሥራ አልነበረኝም። እያደር ጉዳዮች ቀስ በቀስ መምጣት ሲጀምሩ ያለማማረጥ መፍትሔ ለመስጠት መሞከር ጀመርኩ። በትክክለኛ አተያይ ማዘጋጃ ቤቱን በቀጥታ የሚመለከት ባይሆንም ለአመልካቾች መፍትሔ የሚያስገኝ እስከሆነ ድረስ ሳያስተናግዱ መመለስ አይታሰብም ነበር። ከመደበኛ የሥራ ክንውን ይልቅ አገልግሎት የማበርከት ጎኑ እየጎላ መጣ።

እንዲህ እያለ፤ በተለይ ከዓድዋ ምድቤ የማከናውናቸው ሥራዎች በመጀመሪያ ዓዲ አቡን ወደምትባለው አነስተኛ ከተማ ተስፋፍቶ ከዚያም በዓድዋ አውራጃ የሚከናወኑ ጉዳዮችንም የሚጨምር ሆኖ ተገኘ።

በአንድ ወቅት የሙያና የሥራ ክንውን መግለጫ (CV) በአማርኛ ባዘጋጀሁበት ወቅት፤

1) የርስት ካርታዎች ማዘጋጀትና በመሬት ላይ ለሚነሱ ክርክሮች የቴክኒክ ውሣኔ መስጠት፤
2) መንገዶችን ማውጣትና የወሰን ምልክቶችን መትከል፤
3) የንብረት ግምት ማዘጋጀትና ሌሎች የንድፍና የቴክኒክ አገልግሎቶችን መስጠት፤
4) በአምባ ራዕዮ አካባቢ የሚገኘውን ዋናው የዓድዋ ጦርነት የተከናወነበትን ቦታ የሚያሳይ ንድፍ ማዘጋጀት፤
5) ለአህሰአ ወረዳ ዋና ከተማ የሚሆነውን ቦታ መምረጥ፤ ዋና ዋና መንገዶችን ማውጣትና ለልዩ ልዩ መሠረታዊ አገልግሎቶችና የመንግሥት መ/ቤቶች የሚሆኑትን ቦታዎች መመደብ፤
በማለት በዓድዋና በአክሱም ከተሞች የሠራሁትን ላካትት ብዬ አስገብቼ ነበር። እነዚህ ክንውኖች በማዘጋጃ ቤቱ ሹም በቀጥታ የደረሱኝና ያከናወንኳቸው፤ በመደበኛ አጠራር ‘ሥራ’ ሊባሉ የሚችሉት ናቸው። የቀን ተቀን ውሎዬ ግን በእነዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ማንኛውም የከተማ ነዋሪ፤ ከአጎራባች አነስተኛ ከተሞች የሚመጡ ጭምር ምክርና እገዛ ሲፈልግ አስተናግዳለሁ። ይህም በከተሞቹ ውስጥ የራሳቸውን ሥራ የሚያካሂዱ ድርጅቶችንም ይጨምራል። አልሜና አቅጄ ባይሆንም የዚህ ዓይነቱ ስምሪት ‘አገልግሎት’ ሊባል የሚችል ነው። በተለይ በመምኅርነት ከተመደቡት አብረውኝ ከተመደቡት ጓደኞቼ ጋር ሳስተያየው፤ የነሱ በተወሰነ ሰዓት የሚከናወን፤ ተመጥኖ የተሰጠና ከሣምንት ሣምንት የማይዛነፍ ሲሆን፤ የኔ ጠዋት ተነስቼ ቢሮ ስገባ በሚያጋጥመኝ ሁኔታ የሚመራ ነበር። በየአስራ አምስት ቀንም አክሱም ሰንብቶ መምጣትም ከመደበኛ አሠራር የተለየ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲው ሲልከን ምንም ዓይነት የመብት መሰል ጥያቄ እንዳናነሳ አስግንዝቦ ስለነበር ጭምር ተልዕኳችንን በሚገባ ፈጽመን ከመመለስ ውጪ ተከፍተን አናውቅም።

በከተማ ውስጥ እየተዘዋወሩ መሥራት ከብዙ ሰው ጋር ያስተዋውቃል። ቋንቋ ለማወቅም በር ይከፍታል። የነዋሪውንም ማኅበራዊ ኑሮ ቀረብ ብሎ ለማየትም ይረዳል። እግረ መንገዱንም ጥህሎም ሆነ ጉዕሽና ጽራይ ለመቀማመስም ምክንያት ይሆናል። በከተማው ውስጥ የሚከናወነውን እንቅስቃሴ በቦታው ሆኖ ለመመልከትም ሆነ በወሬ ደረጃም ቢሆን ለመስማት ያስችላል። አንድ ቀን በድልድዩ በኩል ሳልፍ ሰዎች ወንዙ ዳር ተሰብስበው ተመለከትኩ። ከላይ ሆኜ ብጠይቃቸው፤ እነሱ ስለሚያውቁኝ ብዙም ሳይከፉ፤ ይልቅ የምትረዳን ነገር ስላለ እናነጋግርህ አሉኝ። በኋላ እንደነገሩኝ በዶክተር አክሊሉ ለማ የሚመራው የቢልሐርዚያ ምርምር ፕሮጀክት የላካቸው ባለሙያዎች እንደሆኑና ካርታ ስሌላቸው የወንዙን ካርታ በተለይም ውሃ ታቁሮ የሚቆይበትን ቦታ ለይቶ በማሳየት እንድረዳቸው ጠይቀውኝ የተቻለኝን ያህል ወንዙን አብሬ እያካለልኩ ንድፍ አዘጋጀን።

እንዲሁ የቅየሳ መሣሪያ ለመዋስ ወደ ማዘጋጃ ቤት የሚመጡ ስለነበሩ፤ መሣሪያው እንደሌለ በመግለጽ ብቻ ሳላበቃ ስለ ሥራቸው በመጠየቅ ቦታው ድረስ ወስደው ያስረዱኝ ነበር። ከአውራ ጎዳና፤ ከፒስ ኮርስና ከመሳሰሉ ተቋሞች የሚመጡት የሚሰሩት ሥራ በዛን ጊዜ ባለኝ ግንዛቤ ብዙም ከወደፊቱ ሙያዬ ጋር የተያያዘ አልነበረም።

አንድ ቀን ግን የማዘጋጃ ቤቱ አዋሳኝ በሆነው የንግሥተ ሳባ ሁለተኛ ደረጀ ትምህርት ቤት ውስጥ ቁፋሮ የሚያከናውኑ ሰዎች አየሁ። ገብቼ ስጠይቅ ሰዎቹ የሥራ ተቋራጭ ሠራተኞች መሆናቸውን በመግለጽ ስለ ሥራው አብራሩልኝ። እየተመላለስኩ ሂደቱን በመከታተልና ብዙ ጥያቄዎችን በማቅረብ ስለ ኮንስትራክሽን ሥራ ሂደት ተረዳሁ። በዚያን ጊዜ ከገረሙኝ ነገሮች መካከል መሠረቱ ተንሳፋፊ (Floating) ነው የሚለው ነበር። በቦታው ላይ የሚጠቀሙባቸውን ሰነዶች ንድፎቹን ጨምሮ ማየት ቻልኩ። ስለ አማካሪና ሥራ ተቋራጭ ግንኙነት፤ ስለልኬትና ክፍያ መጠነኛ ዕውቀት ኖረኝ።

ዓድዋ ከመቀሌ፤ ከአስመራ ወይም ከእንዳሥላሴ አቅጣጫ ተነስተው ለሚጓዙ አውቶቡሶች የምሳ እረፍት የሚደረግባት ከተማ ነበረች። በዚህም ምክንያት ብዙ መንገደኞችን የማግኘት ዕድልም ነበረኝ። በዚያን ሬዲዮ እንኳን በአግባቡ መከታተል በማይቻልበት ዘመን የ1961 ዓ.ም.ን ታሪካዊ ክስተቶችን ማወቅ የሚቻለው ከመንገደኞች ነበር። በዚያን ጊዜ ትኩረቴ በተመደብኩበት ተልዕኮ ላይ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩ ተጓዦች በተለያየ አቅጣጫ ወደ ትግል ሜዳ እየሄዱ እንደነበር አዲስ አበባ ከተመለስኩ በኋላ ነበር ያወቅሁት። ወደ ክረምቱ መግቢያ አካባቢ ግን የመጀመሪያ የሆነችውን ሬዲዮዬን ገዝቼ ስለነበር እንደአጋጣሚ ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ ቢቢሲ ከፍቼ ዜና ሳዳምጥ ኒል አርምስትሮንግ በቀጥታ ከጨረቃ ሲናገር ሰምቼ ተደነቅሁ። በዚህ ሁሉ መካከል፤ በተለይ ከዓመቱ አጋማሽ በፊት በማያስታውቅና ጣልቃ በማስገባት መንገድ ስለ ዓድዋ የድል በዓል አከባበር ምን እንደታሰበ ሳልጠይቅ ቀርቼ አላውቅም። የምርጫ ዘመን ስለነበርም ስለምርጫ ገለጻ ለመስጠት የመጣውን ተዘዋዋሪ ቡድንን ብጠይቅም የሚያውቁት ነገር አልነበረም።

ዓድዋን ለሁለት የሚከፍለውን የአሰም ወንዝ ድልድይን በቀን አንድ ጊዜ ሳይሻገር የሚውል ነዋሪ ያለ አይመስለኝም። የምትፈልገውን ሰው ለማግኘት እዚያ አካባቢ ጥቂት መጠበቅ አለበለዚየም በርሄ መሊጥን መጠየቅ በቂ ነው። በርሄ ከድልድዩ አራት ጫፍ ላይ ካሉት ወፍራም ጉራጅ አምዶች ላይ ተቀምጦ የሚውልና ሂያጅ መጪውን ሠላምታ የሚሰጥ ነው። ከመንበሩ ወርዶ ያየሁት ሁለት ቀን ብቻ ነው። አንድ ቀን እሱ ባለበት በኩል ሳልፍ ‘መሐንዱስ ወደይ ድራረይ እንዶ ሃበኒ’ ብሎኝ ገንዘብ ብሰጠው ወርዶ ትንፋሽ እሰኪያጥረኝ ድረስ ያቀፈኝ ጊዜ ነው። በርሄ ነዋሪውን በሙሉ የሚያውቅና ስለእኔ ጭምር በቂ መረጃና አስተያየት እንደነበረው ስገነዘብ በትንሽ ከተማ ውስጥ ያለውን የመረጃ ፍሰትና አስፈላጊነቱን መረዳት ቻልኩ።

መልስ ያላገኘሁለት የዓድዋ ድል አከባበርን የሚመለከት ምንም ፍንጭ ሳላገኝ የየካቲት ወር ገባ። ከመቀሌም ሆነ ከአዲስ አበባም ሆነ ባለሥልጣን ይመጣ ይሆናል የሚለው ግምቴም አጠራጣሪነቱ እየጎላ መጣ። ምናልባት የማዘጋጃ ቤቱ ወይም የአውራጃ ግዛቱ የሥራ ድርሻ ይሆናል እንዳልል ቢያንስ በማዘጋጃ ቤቱ በኩል ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም።

ሰባ ሦስተኛው የዓድዋ ድል ቀን የዋለው እሑድ ዕለት ነበር። በጠዋት ተነስቼ ከቤታችን በረንዳ ላይ ሆኜ ብመለከት፤ እኔ ከምገኝበት መቃሉም ሆነ ከአሰም ወንዝ ባሻገር ደረቱን ሰጥቶ ከሚታየኝ የጥንቱ ከተማ ምንም እንቅስቃሴ አይታይም። ጓደኞቼ በሙሉ ተኝተው ስለነበር ቁርስ ባለመቅረቡ ሻይ እንኩዋን ሳልጠጣ የዚህን ጉዳይ መጨረሻ አያለሁ ብዬ ወደ ዋናው መንገድ አመራሁ። መንገዱ ጭር ብሏል። ንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት ደርሼ ወደ ድልድዩ እንደታጠፍኩ ግን በፍጹም ያልጠበቅኩት ነገር ገጠመኝ። ጥቂት ሰዎች ተሰልፈው እየዘፈኑ ድልድዩን አልፈው እኔ ወደነበረኩበት መታጠፊያ እያመሩ ነበር። ከመካከላቸው በርሄ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ሲጓዝ ፊቱ ላይ ከዚህ በፊት አይቼው የማላውቀው ጥልቅ ስሜት ይታይበት ነበር። እኔም ሰልፉን ተቀላቅዬ ወደ አውራጃ ግዛት ጽሕፈት ቤት አመራን። እዚያም አውራጃ ገዢው ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ገብረመድህን በተገኙበት ንግግርና አጭር ትርኢት ተደርጎ የበዓሉ ፍጻሜ ሆነ።

ይህን ሁሉ ጊዜ ስጨነቅበት የነበረው የ ‘ኬሮኬ’ ጉዳይም ዳግም ላይነሳ መዝገቡ እንደተዘጋ ተቆጠረ።

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© October, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.