...

The African Building Platform

Trending

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር እና መሀንዲሱ የንጉስ አማካሪ

ህላዊ ሰውነት በሻህ
(አርኪቴክት)
Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on telegram

በንጉስ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ አስቸኳይ ጥያቄ መሰረት በ1871 ዓ.ም. ሶስት የስዊስ ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። የመጡትም ንጉሱ ለሚያስፈልጋቸው የተለያዩ አገልግሎቶች የአውሮፓ ቴክኒሻን እና አማካሪዎችን በመሻታቸው ሲሆን በወቅቱ አፄው የሸዋ ክፍለሀገር ገዢ እንጂ የኢትይጵያ ንጉሰ ነገስት ሆነው አልተሰየሙም ነበር። ከሶስቱ ባለሙያዎች አንዱና ዋነኛው በዙሪክ ፖሊቴክኒክ ትምህርት ቤት የተመረቀው ሜካኒካል መሀንዲስ አልፍሬድ ኢልግ ነበር። አልፍሬድ ኢልግ የኢትዮጵያን ምድር ከረገጠ ጊዜ ጀምሮ ለ28 አመታት በማገልገል የቆየ ሲሆን፣ ከቤተመንግስት ቴክኒሻንነት ተነስቶ የንጉሱ ዲፕሎማሲ አማካሪ ለመሆን የበቃና የአገሪቱን ከፍተኛ የሲቪልና የውትድርና ኮኮብ ሊሻን ተቀዳጅቷል። በታሪክ ምሁራን ዘንድ ኢልግ የኢትዮጵያ ዘመናዊ እድገትና የስልጣኔ ጉዞ ላይ ከፍተኛ አሻራ ጥሎ ያለፈ አውሮፓዊ በመባልም ይታወቃል።

ካለፈው እትም ከቀጠለው በዚህ አምዳችን በ19ኛው ክ/ዘመን ማገባደጃና በ20ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ ላይ ከአዲስ አበባ በመነሳት የኢትዮጵያን ማህበረሰብ የእለት ተዕለት ኑሮ የተቀላቀሉትን የአለማችን ግንባር ቀደም ቴክኖሎጂዎችን እየዳሰስን እንገኛለን። በክፍል አንድ ላይ የስልክና የቴሌኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በአገራችን የተስፋፋበትን ሂደትና በወቅቱ የገጠሙትን ማህበራዊና ባህላዊ ጫናዎች ተመልክተናል። እንዲሁም አጼ ምንሊክ በዚህም ሳቢያ ‘ከሰይጣን ጋር ተዛመዱ’ በመባል የተኮነኑበትን ሁኔታና የማህበረሰቡን ተጽዕኖ ተቋቁመው ስልክን በማስፋፋት በፍጥነት ከክፍለ ሀገር አስተዳዳሪዎች ጋር በመገናኘትና ቁጥጥር በማድረግ የኢትይጵያ ፖለቲካዊ አንድነት ላይ ተጽዕኖ መፍጠር እንደቻሉ አይተናል። በዚህኛው ክፍል ደግሞ አዲስ አበባን ከጅቡቲ ወደብ ጋር በማገናኘት ኢትዮጵያን ከአለም ኢኮኖሚ ጋር ይበልጥ ያስተሳሰረውን የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ኩባንያን አፈጣጠር እንዲሁም ተያያዥ ኩነቶችና ግለሰቦችን እንቃኛለን።

በየካቲት 5, 1885 ዓ.ም. አፄ ምንሊክ የረጅም ጊዜ ረዳታቸውን አልፍሬድ ኢልግን ወሳኝ ተልዕኮ ይሰጡታል። ተልዕኮውም አዲስ አበባን ከቀይ ባህር ጋር በበቅሎ ወይም በግመል ለማገናኘት ስድስት ሳምንታት ይፈጅ የነበረውን ጉዞ በባቡር መንገድ ለመተካት የሚቻልበትን ሁኔታ በማጥናት የግል ኩባንያ እንዲያቋቁም ነበር። ትዕዛዙም እንዲህ ይላል፤

“ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገስተ ዘኢትዮጵያ፤ በዚህ ደብዳቤ ሙሴ አልፈሬድ ኢልግን እስከዛሬ ድረስ ብዙ ዘመን ሲያገለግለኝ የኖረ መሐንድሳችን ሎሌአችን በሐገሬ ንግድና ጥበብ ለማስፋት መንገድ ካልተበጀ እንዳይቀና ስለ አወቅሁት የጢስ ሰረገላን ባገሬ ለማቆም ብፈልግ ለዚህ ባቡር የሚያስፈልገውን ጉዳይ ሁሉ ለመፈጸም ትልቅ ኩባንያ ለማውጣት እንዲመረምር ፍቃድ ሰጥቸዋለሁ። በየካቲት በ፭ ቀን ባዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ በ፲፰፻፹፭ ዓመተ ምሕረት።”
ኢልግም ጥናቱን በመፈጸም በአመቱ መጋቢት ወር 1886 ዓ.ም. ላይ ከፈረንሳዊ ባልደረባው ሊዮን ሼፍኖ ጋር በመሆን ዋና መስሪያ ቤቱን በፓሪስ ከተማ ያደረገ “የኢትዮጵያ ኢምፔሪያል የባቡር ኩባንያ” የሚባል ድርጅት ያቋቁማል። አፄ ምንሊክም ለኩባንያው የባቡር መስመሩን እንዲያስገነባ እና ለ99 ዓመት የባቡር አገልግሎትን በማቅረብ እንዲንቀሳቀስ ፈቃድ ይሰጡታል። በተራውም ኩባንያው ለንጉሱ አክሲዮን እና ከሶስት ሚሊዮን ፍራንክ በላይ ትርፍ ሲያገኝ ግማሹን ለመስጠት ይስማማል። የኩባንያውን ምስረታ እንደተጠናቀቀ ኢልግ ወደ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ሲመለስ፣ ባልደረባው ሼፍኖ ደግሞ ለኩባንያውና ለባቡር ሀዲዱ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሀብት ለማሰባሰብ ወደ ፈረንሳይ፣ ቤልጅየም እና እንግሊዝ ያቀናል።

አልፍሬድ ኢልግ – ከቀኝ ሁለተኛው – Image: African Train

ታሪክ ተገጣጠመ እንዲሉ ሆነና፣ የባቡር ኩባንያው በተቋቋመ በሁለት አመቱ ኢትዮጵያ ከጣሊያን የቅኝ ገዢ ጦር ጋር በአድዋ ተራሮች ላይ ትፋለምና በየካቲት 1888 ዓ.ም. ድል ትጎናጸፋለች። ይህን ተከትሎም የአለም ሀያላን መንግስታት ለአገሪቷ ሉአላዊነት እውቅናቸውን ይሰጣሉ። ኢትዮጵያና ፈረንሳይም በዛው አመት በግንቦት ወር ላይ የጅቡቲ ወደብን ለኢትዮጵያ ንግድ “ህጋዊ መተላለፊያ” ለማድረግ የወዳጅነት ስምምነት ይፈጽማሉ። ኩባንያው ወደ ስራ ለመግባት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ያጠናቅቃል። ነገር ግን የባቡር ሃዲድ ግንባታው በቀጣይ ከፍተኛ የፖለቲካ፣ የገንዘብና የዲፕሎማሲ ፈተናዎች የሚገጥሙት እና በተለያዩ ምክንያቶች እጅግ የተንጓተተ ግዙፍ ፕሮጀክት ይሆናል።

በመጀመርያ የባቡሩ ኩባንያ ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ በአውሮፓ ዙርያ አክስዮን ለመሸጥ ይቸገራል። ከአክስዮን ሽያጩ የተገኘውም ገንዘብ ለግንባታው የሚበቃ ባይሆንም የባቡር ሀዲዱ ግንባታ ስራ በጥቅምት ወር 1890 ዓ.ም. በጅቡቲ ወደብ ላይ ይጀመራል። በሌላ በኩል ከኩባንያው አክስዮን ጋር ተያይዞ የፈረንሳይ መንግስት ፍላጎት በማሳየቱ የኢትዮጵያና የእንግሊዝ መንግስታት ይቆጣሉ። ኢትዮጵያ ወደፊት ከፈረንሳይ ሊመጣባት የሚችል ተጽዕኖን በመስጋት፣ እንግሊዝ ደግሞ በሶማሌ ሀገር የሚገኘው የዘይላ ወደቧን ጥቅም ስለሚጋራባት ተቃውሟቸውን በአደባባይ ያሰማሉ።

በሁለተኛ ደረጃ፣ የፕሮጀክቱ ግንባታ ከጅቡቲ ወደብ ተነስቶ የመጀመሪያው ምዕራፍ ማጠናቀቂያ የሆነው የኢትዮጵያ ድንበር ላይ ከመድረሱ በፊት ሌላ የፋይናንስ ቀውስ ይገጥመዋል። ይህም እራሳቸውን “አዲሱ የአፍርካ ኩባንያ” በማለት የሚጠሩ የእንግሊዝ ባለሀብቶች አዲስ የገንዘብ ምንጭ ይዘው በመምጣት ኩባንያውን ለረጅም አመታት ይቆጣጠሩታል። የፈረንሳይ ባለሀብቶች ኩባንያው ላይ የነበራቸውን ሀይል ለመጠበቅ ቢጥሩም አልተቻላቸውም። ሁለቱም መንግስታት የኢትዮጵያን ንግድ በበላይነት የመቆጣጠር ፍላጎት ስለነበራቸው እርስ በርስ ይገፋፋሉ። በመጨረሻም የእንግሊዝና የፈረንሳይ ኢንቬስተሮቹ በጋራ ለመስራት አዲስ “አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ባቡር ትረስት እና ግንባታ ኩባንያ” የሚባል ድርጅት ይመሰርታሉ።

ጅቡቲ የሚገኘው ባቡር ጣቢያ – Image: African Train

የሁለቱ አገራት ፍላጎትና ዛቻ አፄ ምንሊክን ያሰጋቸዋል። በተለይ የፈረንሳይ መንግስት ሳያሳውቃቸው እና የኩባንያው ውለታ ላይ ያሉ በርካታ አንቀፆችን በመጣስ፣ ንጉሱ በባቡሩ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ለማሳነስና የራሳቸውን ከፍ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ ያበሳጫቸዋል። ስለሆነም የባቡር ሀዲድ ፕሮጀክቱን ቀጣይ ምዕራፍ የሆነው ከድሬዳዋ እስከ አዲስ አበባ ከተማ የሚደርሰው ግንባታ እንዲቆም ያደርጋሉ። የባቡሩ የድሬዳዋ ጣቢያ ምረቃ ስነስርዐት ላይም ሳይገኙ ይቀራሉ። ፈረንሳዮቹ ስራ ለመቀጠል ድርድር ለማድረግ ቢጥሩም ንጉሱ አመኔታቸው የበለጠ እየቀነሰ ስለመጣ በማገዳቸው ኩባንያው የብድር እዳውን መክፈል እያቃተው ይመጣና ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ይወድቃል።

የተከሰተውን አለመግባባት ለመታፍት ሲባል ድርድሮች ይደረጉና አፄ ምኒልክ ለሙሴ አልፍሬድ ኢልግ ሰጥተውት የነበረውን የምድር ባቡር ስራና ፈቃድ በምትኩ የግል ሀኪማቸው የሆነው ዶ/ር ጆሴፍ ቪታሊዬ ወኪል ሆኖ እንዲሰራ ይፈቅዳሉ። በነሐሴ 2፣ 1896 ዓ.ም. አፄ ምንሊክ አዲስ አበባ፡ለሚገኘው የፈረንሳይ እንደራሴ በፃፉት ደብዳቤ የባቡር ኩባንያው አላስፈላጊ ጊዜ እንዳይባክንበት በማለትም ከድሬዳዋ ተነስቶ እስከ አዲስ አበባ የሚደርሰውን የፕሮጀክቱን ቀጣይ ምዕራፍ ግንባታ እንዲቀጥል ፈቃዳቸው መሆኑን ይገልፃሉ። ይህን ተከትሎም በታህሳስ 4፣ 1899 ዓ.ም. እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን በለንደን ከተማ ኢትዮጵያን በሚያከብር ሁኔታ በተፈራረሙት የሶስትዮሽ ስምምነት ላይ የባቡር መስመሩ ግንባታ መቀጠልን በመደገፍ፣ ነገር ግን ስራው ወይ በቀድሞው የኢትዮጵያ ባቡር ኩባንያ ወይ በሌላ የፈረንሳይ የግል ኩባንያ አማካኝነት እንዲጠናቀቅና የሶስቱ ሀገር ዜጎች የባቡር አገልግሎትና የነጻ የቀረጥ ታክስ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይወስናሉ። ስለሆነም በቀጣይ የቀድሞው ኩባንያ ይፈርስና ንብረቱ ተላልፎ በአዲስ “የፍራንኮ ኢትዮጵያ ባቡር” በተባለ ድርጅት እንዲተካ ይደረጋል።

የባቡር ሀዲዱ ግንባታ በመቀጠል ከተጀመረ ከሁለት አስርተ አመታት በኋላ በ1910 አዲስ አበባ ይደርስና ይጠናቀቃል። በአፄ ምንሊክ የተጀመረው ግንባታ በንግስት ዘውዲቱ ይመረቃል። የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ኢትዮጵያን ከባህር በር ጋር በብቸኝነት በማገናኘት ባገለገለባቸው ረዥም አመታት አገሪቷን ለውጪው አለም ተደራሽ እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሲያበረክት፣ የኢኮኖሚና የጦር ሀይል ተወዳዳሪነቷን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮታል።

የድሬዳዋ ባቡር ሀዲድ – Image: African Train

የኢትዮ – ጅቡቲ ባቡር እስከ 1940ዎቹ ድረስ የኢትዮጵያ ዋነኛ የትራንስፖርት ሰንሰለት ሆኖ በማገልገል ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በሃላ ቀስ በቀስ የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት መስፋፋትን ተከትሎ የባቡር መስመሩ ፋይዳ እየቀነሰ መጥቷል። የድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ በመስመሩ ዳርቻ በርካታ ከተሞች እንዲፈጠሩ መንስኤ እንዲሁም የኢትይጵያ የነጻነቷ ተምሳሌት እና የሀገር ኩራት ምንጭ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል።

የኢትዮ – ጅቡቲ ባቡር በ20ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረውን የአለም የሀያላን ፉክክር፣ የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችና ተጽዕኖዎች እንዲሁም የገንዘብ ፈተናዎችን በማለፍ ኢትዮጵያን ከአለም የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ጋር ያስተሳሰረ የወቅቱ ግዙፍ ፕሮጀክት ነበር። አሁን ባለንበት የ21ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያውያን ሀብት የሚገነባውና የሀገር ኩራት ፕሮጀክት የሆነው የህዳሴ ግድብም ተመሳሳይ ሊባሉ በሚችሉ ውጫዊና ውስጣዊ ትግዳሮቶች በመፈትን እና ችግሮቹን ተቋቁሞ በመገባደድ የአፍሪካ ትልቁ ግድብ ለመሆንና ሀይል ለማመንጨት ጫፍ ላይ ይገኛል። አንዳንዴ ታሪክ እራሱን ይደግማል እንደሚባለው ይሆን?

ራስ ተፈሪ የድሬዳዋ አዲስ አበባ ሀዲድ የምረቃ ጉዞ ሲያደርጉ Image: African Train

በሚቀጥለው አምድ ሌላኛው የአፍሪካ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድና የአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፍያን ታሪካዊ አመጣጥ እንዳስሳለን። ቸር እንሰንብት!

Twitter @HelawiSewnet helawi.sewnet@gmail.com

Interesing article?

Check out the full journal for other interesting contents and more.

Thank you for reading Ketema, the African building platform.

Subscribe below to receive an email when a new issue is released.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

© October, 2024 Ketema Journal

Thank you for reading Ketema, the urban building platform.

Subscribe below to receive an email when a new bimonthly issue is published.

Your email address will not be shared with anyone else, and it’s easy to opt out if you change your mind.

Seraphinite AcceleratorOptimized by Seraphinite Accelerator
Turns on site high speed to be attractive for people and search engines.